Ethiotelecom Logo

የስራ ባህላችን


የስራ ባህላችን

ቆየት ያለ አንድ ተረት ወደ አዕምሮዬ መጣ ፤ በጥንት ጊዜ አንድ ሰዉ ነበር ይሄ ሰዉዬ ዘወትር እህል በገዛ ቁጥር ወይም እህል ከአዉድማ ባስገባ ጊዜ በቅርብ የነበሩት አጎቱ ጋር እየሄደ የፍየል ስልቻ ይለምናል:: አጎትዬዉም በሰዉዬዉ ድርጊት ሁሌ ይደነቁ ነበር እናም ይሄ ስንት ፍየል ከነ መቅኔዉ ቀርጥፎ የመጠጠ ሰዉ አለማሰብ ነዉ እንጂ እንዴት የራሱ አንድ እንኳን ስልቻ ያጣል ብለዉ አሰቡ ፤ ያልማደኛ ሰዉ ከተወሰነ ቀናት በኋላ ያመረተዉን ሰብል ከአዉድማ ወደ ቤት ለማስገባት ብሎ መቋጠሪያ ስለቸገረዉ እንደተለመደዉ አጎቱ ጋር ሩጫዉን ጀመረ ፤ አጎቴ አስኪ እባክዎት አንድ ሁለት ስልቻ አበድሩኝ እህሉን ካስገባሁ በኋላ እመልሳለሁ ብሎ ጠየቃቸዉ ፤ የአጎትዬዉ ምላሽ ግን አስገራሚ ነበር ፤ እየዉልህ ልጄ በር ላይ የቆሙት የፍየል ወጠጤዎች ይታዩሀል አሉት ፤ ሰዉዬዉም እነርሱ አካባቢ አለ ሊሉት መስሎት ቸኮል ብሎ አዎን አለ ፤ አጎትዬዉም በል ደስ ያለህን ሙክት መርጠህ ይዘህ ሂድ አሉ ፤ ሰዉዬዉም ተደናግጦ አጎቴ ፍየል እኮ አላኩዎትም የፍየሉን ስልቻ እንጂ አለ ፤ አየህ ልጄ አንተ ካሁን በኋላ የራስህ ነገር ሊኖርህ ይገባ ሁሌ የእኔን እጅ ማየት የለብህም ስለዚህ ከፍየሉ ስልቻ አዉጥተህ ተጠቀም ብለዉ ሸኙት፡፡ ነጮቹ እንደዚህ ይላሉ ለጓደኛህ እዉነተኛ ወዳጁ ከሆንክ አሳዉን እያጠመድክ ከመስጠት ይልቅ ፤ ማጥመጃ ገዝተህ ስጠዉ ቀጥሎም አጠማመዱንም አሳዬዉ ይላሉ፡፡

          በሀገራችን ልክ እንደ አጎትዬዉ ሰዉ በራሱ ጥረት ራስን እንዲችል ከማድረግ ይልቅ ስልቻ የማበደሩ ባህል የተለመደ ነዉ ፡፡ አንድ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ የወጣ ልጅ የራሱን እቅድ ነድፎ የሚንቀሳቀስበት ገንዘብ ከምንደጉመዉ ይልቅ ያለንን ጥሪት ለቃቅመን ለክብራችን ስንል ላንድ ቀን በሬ ጥለን ከሀገሬዉ ጋር ፍሪዳ በሚጥሚጣ ስንቆርጥ መዋል ይቀናናል፡፡ ያልጅ ወደ 17 ዓመት ሲማር እንኳን ስልክ ሊደዉልለት ቀርቶ መማሩ እንኳን ያላወቀ ሁሉ የምርቃቱን ስነ-ስርዓት ቀን አበባዉን ተሸክሞ ይግተለተላል፡፡ በሁለተኛዉም ቀን ሀገሬዉም ወደ እያለበት ልጁም ወደ የማያባራዉ እና እልህ አስጨራሹ የሥራ ፍለጋ ይሰማራል፡፡

          ልጆቻችንን እንዴት ነዉ የስራ ባህል የምናስለምዳቸዉ ? አስታዉሳለሁ ህፃን እያለን አባታችን እኔና ወንድሞቼ ስራ ስንሰራ እየተፎካከርን አስቸገርን  ፤ ትንንሽ እንደ ካልሲ የመሰሉ ልብሶች የሚያጥባቸዉ ጠፋ ፤ ጫማ አፅድቶ የሚቀባዉ አጣ ፤ እናታችን ካለሆነች ቤት የሚወለዉል ልጅ ጠፋ በመጨረሻም ያደረገዉ ነገር እስካሁን ያስደንቀኛል እኔ እና ሁለት ወንድሞቼን ጠራን እና እየዉላችሁ ልጆች ከዛሬ ጀምሮ ካልሲ ለሚያጥብ በአንድ ካልሲ 20 ሳንቲም ፤ ጫማ ለሚቀባ ( ቀለሙን እና ብሩሽ ተችሎለት) አንዱን 50 ሳንቲም ፤ ቤት ለሚወለዉል እና እቃ ለሚያፀዳ 2 ብር አለዉ ብሎ ተመን አወጣ ፤ መጨረሻም አብረን እንድንሰራ ብሎ ብር በየግል አይሰጣችሁም ፤ የእለቱን ደምራችሁ ወር ላይ ደሞዝ ሲወጣ ጠይቁ ገንዘቡን እዚህ የምታዩት የቁጠባ ሳጥን ዉስጥ ይቀመጣል ከዚያ ስትፈልጉት ትጠቀሙታላችሁ አለን ፤ እኛም ሳናቅማማ ወዲዉኑ ስራ ጀመርን፡፡ ከዚያ ቀን ጀምሮ የታጠበ ካልሲ ድጋሜ ይታጠብ ጀመረ ፤ ጫማ ሁሉ አቧራ በነካዉ ቁጥር መወልወል ሳይሆን መቀባት ጀመረ ፤ ያ በሳምንቱ የሚወለወል ቤት ቶሎ ቶሎ መፀዳት ጀመረ ፤ በዚህ ሁኔታ አራት ወራት አለፉ እና እኛም ብሩን ስለምንፈልገዉ ይዉጣልን ብለን ለበላይ አካል ጥያቄ አቀረብን ፡፡ ከበላይ አካል አዎንታ እንዳገኘን ሳጥኗ ተከፈተች ፤ አላመንንም ሳንጠብቃት ካቅሟ በላይ ነበር የያዘቸዉ 220 ብር ፤ ዘመኑ አሁን የማንገለገልባት አምስት ሳንቲም እንኳን ከረሜላ የመግዛት አቅም ነበራት ፤ በ 1 ብር ከረሜላ ሳይሆን 4 እንቁላል ይገዛበት ነበር ፤ 30 ብር እንዳሁኑ የሽሮ ሳይሆን የዶሮ መግዣ ነበር ፤ ባጭሩ በወቅቱ 220 የአንድ አነስተኛ ገቢ ያለዉ ሰራተኛ የወር ደሞዝ ነበር እናም ይሄ ብር ለእኛ የማይታመን ነበር ፤ ልብ በሉ እዚህ ጋር አባቴ ሁለት ወፍ በአንድ ድንጋይ ነዉ የመታዉ የመጀመሪያዉ ልጆቹን የሥራ ጥቅም እንድንረዳ ሲያደርገን ሁለተኛዉ ደግሞ የቁጠባ ሳጥን በማዘጋጀት የቁጠባ ባህልን እና ጥቅም አስተምሮናል፡፡

          እዉነት ለመናገር በስራ ፈጠራ እና በስራ ባህላችን ዙሪያ ያለን ግንዛቤ ገና ብዙ ይቀረናል ፤ ከቤታችን ቀጥሎ ሱቅ ከተከፈተ እኛም ሱቅ እንከፍታለን ፤ ስጋቤት ከሆነ ደግሞ ስጋቤት፡፡ ለነገሩ ሙሉ ለሙሉ በእኛ አይፈረድም የትምህርት ፖሊሲያችን ዉስጥ ኢንተርፕረነርሽፕ የሚል ነገር ዘሎታል ይሄም የተማርነዉን ሳይንስ እንደ ዉሀ ጠጥተን ከማንበልበል ፤ ምንም ሳንሰራበት በድግሪ ላይ ድግሪ ከመደረብ ፤ ወረቀት ከመለቃቀም ዉጪ በተግባር ጠብ የሚል ነገር ለህብረተሰባችን ብሎም ለእኛ ፋይዳ ያለዉ ነገር እንዳንሰራ አድርጎናል፡፡ ቤተሰቦቻችንም ትምህርት ቤት ሄደን ፊደል ቆጥረን እንድንመጣ ከማድረግ ዉጪ የቢዝነስ ፣ የስራ ፈጠራ ፣ መክሊታችንን የመከተል ፣ ራስን የመምራት ፣ ችግሮችን በብልሀት የመፍታት ጥበብ የመሳሰሉትን ነገሮች የማዉረስ እና በልጆቻቸዉ የማስረፅ ነገር አልተለመደም፡፡

          ከላይ የተጠቀሱት እና በተለያዩ ተጨማሪ ምክንያቶች የስራ ባህላችን የወረደ ነዉ፡፡ ለአብዛኞቻችን ስራችን አለቃችን አይደለም ፤ ለክፍያ ወይም ለበላይ አለቆቻችን ስንል ብቻ ነዉ የምንፈፅመዉ፡፡ የተወሰነ ጊዜያትን ተቸግረን የራሳችንን ነገር ይዘን ከመቆም ይልቅ የሰዉ ተቀጣሪ ሆነን ብዙ ሳንለፋ እየተሹለከለክን ገቢ ማግኘትን እንመርጣለን ፡፡

          የሀበሻ ጀብዱ በአዶልፍ ፓርለሳክ ተፅፎ በተጫነ ጆብሬ መኮንን የተተረጎመ ድንቅ ኢትዮጵያዊ መፅሀፍ ነዉ፡፡ አዶልፍ ፓርለሳክ ለኢትዮጵያ ፍቅር ህይወታቸዉን ለመሰዋት ዝግጁ ከነበሩ እና ኢትዮጵያን ልባቸዉ እስኪጠፋ ከሚወዱ ነጮች አንዱ ሲሆን በዘመነ ሀይለስላሴ ጣልያንን የተዋጋ ኢትዮጵያዊ ደመ ነፍስ ያለዉ ሰዉ ነወ፡፡

          አዶልፍ ፓርለሳክ ገና በዚያን ግዜ ኢትዮጵያን “እንቅልፍ ላይ ያለች ሀገር” ብሎ ነበር የሚገልፃት፡፡ የዜጎቿ ደካማ የሥራ ባህል ሁል ጊዜ ያበሳጨዉ ነበር፡፡ በመፅሀፉ ላይ ገፅ 30 የሚከተለዉን አገላለፅ ተጠቅሞ ምን ያህል ደካማ የሥራ ባህል እንደነበረን ትዝብቱን ያወጋናል፡፡

“ከዛሬ አምስት አመት በፊት ማለት በመጀመሪያዉ በኢትዮጵያ ጉብኝቴ እነዚህ ወዶ ገባ ባሮች በስራ ላይ እንዳሉ የማየት እድሉ ገጥሞኝ ነበር፡፡ አዎ እነዚህ ባሮች ለጌታቸዉ የድንጋይ ቤት ለመስራት ድንጋይ እየለቀሙ ነበር፡፡ አስራ አራት ቀን ሙሉ ለቤት መስሪያ የሚሆን ድንጋይ ከአካባቢዉ እየፈለጉና እያመጡ ቤት ሊሰራበት ከታሰበዉ ቦታ ላይ ይከምራሉ፡፡ የነዚህን ባሮች አስራ አራት ቀን ስራ የአዉሮፓ ሁለት ወዛደሮች በአንድ ቀን ይሰሩት ነበር፡፡

ብቻ እነዚህ 20 የሚሆኑ ባሮች አስራ አራት ቀን ሙሉ እያንዳንዱ ባሪያ አንድ ሰዓት ሙሉ ድንጋይ ሲፈልግ ይቆይና በጣም አነስ ያለች ድንጋይ ሲያገኝ እሷኑ ያንጠለጥልና አምጥቶ ከዚች የድንጋይ ክምር ላይ ይወረዉራትና ከጓደኞቹ ጋር ተቀምጦ ሁለት ሰዓት ያወራል፡፡”

          አዶልፍ ፓርለሳክ ገና በዚያን ጊዜ የነበረን ደካማ የሥራ ባህል ምን ያህል ከዘመኑ ወደ ኋላ እንሚያስቀረን ለመገመት አላደገተዉም፡፡ አሁንም በመንግስት ደረጃ እንኳን የአንድ ሰዉ አማካይ የሥራ ሰዓት 8፡00 ሰዓት በቀን ፤ በሳምንት ደግሞ ካሉት 168 ሰዓታት ዉስጥ 44 ሰዓታትን ብቻ እየተሰራ ፤ ከዚሁ ላይ በስብሰባና በግል ጉዳይ እየተቀናነሰ እንዴት ሆኖ ነዉ ከሌሎች የአዉሮፓ እና ኤዥያ ሀገራት ጋር በእድገት መፎካከር የምንችለዉ ?

          የስራ ባህላችን በጣም ደካማ ነዉ ፤ በ1990ዎቹ ነዉ ፡፡ ጊዜዉ ቻይና በኢትዮጵያ አሁን እግሯን እና እጇን በሰፊዉ አንፈራጣ እንደ እንቦጭ አረም ለመስፋፋት ጠብ እርግፍ የምትልበት ነበር እና በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ መንገድ ፕሮጀክቶች ላይ ተሰማርታ የነበረበት ወቅት ነዉ፡፡ እናም በዚያም ወቅት የተለያዩ ኢትጲያዉያን በእነዛ የቻይና ካምፓኒዎች ስር ተቀጥረዉ ይሰሩ ነበር ፤ ነገር ግን የቻይኒቲን የስራ ጫና መቋቋም ያልቻሉት የኛዉ ሀገር የቀን ሰራተኞች የያዙትን አካፋ ከመዛቂያነት ይልቅ ብብታቸዉ ስር እየሸጎጡ መመርኮዣ ብሎም ማንቀላፊያ አደረጉት በዚህም ድርጊት የተበሳጩት መላ የማያጡት ቻይናዉያን አካፋዉ የሰራተኞቻቸዉ ብብት ጋር እንዳይደርስ አሳጥረዉ ቆርጠዉ መጨረሻ ላይ ለመያዝ እንዲያመች መያዣ ያለዉ ድንክዬ አካፋ አዘጋጁላቸዉ ፤ ሰዉ አስተሳሰቡ ካተለወጠ ብሎም ለስራ ተነሳሽነት እና ልምድ ከሌለዉ ከባድ ነዉ፡፡ ምንም እንኳን አካፋዉ ቢያጥርም እነዛ የቀን ሰራተኞችም እንደ ቻይኖቹ የአፀፋ ምላሽ አላጡም ፤ ያቺን አጭር አካፋ መሬት ላይ ይሰኳት እና መያዣዋ ላይ ቁጭ እያሉ ይዉሉ ጀመር ፤ በመጨረሻም ቻይኖቹ በጣም ተበሳጭተዉ የአካፋዋን መያዣ በመንቀል ጫፏን ለመቀመጥ የማይመች ሹል አድርገዉ አዘጋጁት፡፡ ከዚህም ይባስ ብሎ ለግንባታ የተዘጋጁ የተለያዩ እቃዎችን ለግል ጥቅማቸዉ ያሸሹ ነበር በዚህም ምክንያት ነበር ቻይናዊያን እነዚህ ሰዎች ሌላ ሀገር አላቸዉ እንዴ ብለዉ እስከ ማማት ያደረሳቸዉ፡፡ ይሄም ለስራችን እና ለህሊናችን ሳይሆን ለአለቆቻችን እና ለጥቅማችን ባሪያ እንደሆንን ማሳያ ነዉ ፡፡

          እኛ ኢትዮጵያዉያን የምንታወቀዉ በደካማ ስራ ባህላችን ነዉ፡፡ ነገር ግን አሜሪካ ሀገር ቆይቶ የመጣ የማዉቀዉ ሰዉ ያወጋኝ የተገላቢጦሹን ነዉ፡፡ እኛ ኢትጲያዉያን አሜሪካን ሀገር የምንታወቀዉ ስራ ባለመናቅ እና በጠንካራ የስራ ባህላችን ነዉ ፡፡ በተለይ በዲቪ የተጓዝን ኢትዮጵያዉያን ኑሮን ለመቋቋም ስንል የማንሰራዉ ስራ የለም ፤ ቀን ከሌት ስራ ነዉ እንቅልፍ አጥተን ነዉ የምንኖረዉ ፤ ነጮቹ የሚጠሉትን ሽንትቤት ማፅዳት እና የጃጁ ሽማግሌዎችን መንባከብ እንኳን አይቀረንም ፤ በዚህ ምክንያት የስራ ቀጣሪዎች ለሀበሻ ሰራተኞች ቅድሚያ ይሰጣሉ ብሎኝ አረፈ፡፡ ሀገራችን ላይ ሀሞታችንን ምን አፈሰሰዉ ? ወኔያችንን የበላዉ ጅብ ምነዉ በዚያዉ ወጥቶ ድምጥማጡ ጠፋ ?

          ብቻ ግራም ነፈሰ ቀኝ የስራ ባህላችን ደካማነት ላይ የማይስማማ አይኖርም፡፡ ቀጣዩ ነገር እንዴት ሆኖ ነዉ ይሄን ነቀርሳ ከአብዛኛዉ ማህበረሰብ ላይ መንቀል የሚቻለዉ የሚሆነዉ ጥያቄ ነዉ፡፡ ጥያቄዉን መመለስ ከተሳነን አለም በሮኬት ፍጥነት ስትምዘገዘግ እኛ በፈረስ እየገሰገስን እጅግ ተራርቀን የዛሬ 50 ዓመት ልክ እኔ አዶልፍ ፓርለሳክ በአፄ ሀይለስላሴ ጊዜ የፃፈዉን ፅሁፍ እንደጠቀስኩት ሌላዉ ተረኛ ደግሞ ይሄንን ፅሁፍ ይጠቅስ ይሆናል፡፡


Reviews

Post Comment