የዘንድሮ ቢዝነስ
ዉሎ እንዴት ነዉ ፤ አንዴትስ እያለፈ ነዉ በእኔ በኩል የስራ ቀን እንደመሆኑ ደፋ ቀና እያልኩኝ ነዉ፡፡ በእኔ በኩል ዛሬ ከማከብራቸዉ እና ብዙ ከተማርኩባቸዉ ጓደኞቼ ጋር ተስፋ የሰነቅንበትን እና ለኢትዮጵያዉን ያለምንም ክፍያ የቴክኖሎጂን ትምህርት በነፃ ለማድረስ ያቋቋምነዉን የኩራዝ-ቴክ (www.kuraztech.com) ፕላትፎርም የተሻለ ለማድረግ እየሰራን እንገኛለን፡፡ እናም በዚህ ምክንያት ዛሬ ብዙዎቻችን ተዕፅኖዉን ስላልተረዳነዉ ነገር ግን ዓለምን እየሾፈራት ስለሚገኘዉ የፕላትፎርም ቢዝነስ ምንነት ትንሽ ልፅፍ ወደድኩኝ፡፡
ከ 100 ዓመት በፊት ዓለም ትኩረቷ ሁሉ ወደ ኢንደስትሪ መር እንቅስቃሴ ነበር፡፡ እጅግ ብዙ ነገሮች በተለይ ከመካኒካል ጋር የተያየዙ ዓለም እስካሁን የምትጠቀምባቸዉ ነገሮች ሁሉ የተፈጠሩበት ድንቅ ጊዜ፡፡ አሁን ባለንበት ጊዜ ደግሞ በተለይም የክፍለዘመኑ ምርጥ ፈጠራ ብዬ አፌን ሞልቼ የምናገርለት ኢንተርኔት ከመጣ ጀምሮ አለም ከመንደርም ቀርባ ጎረቤት እንድትሆን ሲያስችላት ፣ ፈጠራዎች ደግሞ ከመካኒካልነት ወደ የማይነካ እና የማይዳሰስ ሶፍትዌርነት እንዲያተኩሩ ሆኗል፡፡
ዛሬ ላይ አዲስ አበባ ላይ ያለ አንድ ባለሙያ ቤቱ ቁጭ ብሎ አሜሪካ ዉስጥ የሚገኝ ትልቅ ካምፓኒ ሰራተኛ ሆኖ እየሰራ ክፍያዉን የሚቀበልበት ፣ ቂርቆስ ላይ አሲድ የደፋ በኢንተርፖል ከአዉሮፓ ተቀፍድዶ ተመልሶ ቂርቆስ የሚታሰርበት ዘመን ነዉ፡፡ ስልካችንን ብቻ ተጠቅመን ሶማሌ ተራ ሳንሄድ ያማረንን መኪና ፣ ቀልባችንን የሳበዉን ቤት የምንገበያይበት ፣ ጥበቃ ሳይኖረን አዲስ አበባ ላይ ሆነን የሐዋሳ ንብረታችንን ደህንነት በስልካችን የምንከታተልበት ፣ ምድር ላይ የተደበቀ ነገር አለ ለማለት የሚያስቸግርበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡
ቴክኖሎጂ ትልቅ አሻራ እና ተዕፅኖ ካሳደረባቸዉ ዘርፎች ዉስጥ አንዱ እና ዋነኛዉ ቢዝነስ ነዉ፡፡ ቴክኖሎጂ ከሚዳሰሱ በፈብሪካ ዉስጥ ግብዓቶችን ተጠቅመን ከምናመርታቸዉ ምርቶች ይልቅ በኮምፒዉተሮች አማካይነት የሚሰሩ እና የሚተገበሩ ሶፍትዌሮች ገበያዉ ላይ ፈርጣማ ጡንቻቸዉን እንዲያሳርፉ አድርጓቸዋል፡፡
ፕላትፎርም የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን አንድ ጋር አጣምሮ የሚይዝ ሲሆን በስሩም የተለያዩ መተግበሪያዎች እና የቴክኖሎጂ ዉጤቶችን የያዘ ባለ ብዙ አማራጭ (MULTISIDED) ቢዝነስ ስትራቴጂ ነዉ፡፡
የፕላትፎርም ቢዝነስ ገቢ ለማስገኘት ሁለት አይነት ገፅታዎች ዓሉት የመጀመሪያዉ ምርት (PRODUCT) ሲሆን ሁለተኛዉ አገልግሎት (SERVICE) ነዉ፡፡ ምርት የምንለዉ ለምሳሌ የተሰሩ የተለያዩ እንደ ማይክሮሶፍት ዊንዶዉስ ያሉ ሶፍትዌሮችን በመሸጥ እና በማከራየት የሚገኝ ገቢ ሲሆን አገልግሎት የምንለዉ ደግሞ እንደ ማህበራዊ ሚዲያዎች ያሉ አገልግሎቶችን በማቅረብ ገቢ የማግኛ መንገድ ነዉ፡፡
ብዙ የቢዝነስ ኢንዱስትሪዎች እና ድርጅቶች እጅ ሰጥተዉ የነበራቸዉን ክብር ለቀዉ ከገበያ ሲርቁ ፤ ከዚህም አልፈዉ ለሌሎች ድርጅቶ ለሽያጭ ሲዳረጉ ሲብስም ከስረዉ ሲዘጉ ፤ ሌሎች ከራዕይ ዉጪ ምንም ገንዘብ ያልነበራቸዉ ደግሞ አንፀባርቀዉ ሲወጡ እና በገፍ ሲያተርፉ አይተናል፡፡ ለእነዚህ ስኬታማ ድርጅቶች የጀርባ አጥንታቸዉ ቴክኖሎጂን በተለይም ማህበራዊ ሚዲያን የተጠቀሙበት መንገድ መሆኑ አያወላዳም፡፡ ቀደም ብሎ ቢዝነስ ፤ ቢዝነስ ለመባል 2 ነገሮች መያዝ ይጠበቅበት ነበር እነሱም የሰዉ ሐይል እና ጥሬ እቃ (RESOURCE) ነበሩ አሁን ግን 3ኛ ነገር ማለትም ቴክኖሎጂን ያልያዘ ቢዝነስ ተወዳዳሪ መሆን እና ራሱን ችሎ መቆም አይችልም፡፡
በፕላትፎርም ቢዝነስ ላይ ንጉስ ሆኖ መቅረት እጅግ ከባድ ነዉ፡፡ ምንጊዜም የተሻለ አማራጭ እና ብዙ ደንበኞች ያሉት ፕላትፎርም አሸናፊ ነዉ፡፡ ዛሬ ላይ ያለ የማይነካ ግዙፍ ፕላትፎርም ነገ በሚመጣ ቤሳቤስቲን በሌለዉ ነገር ግን እጅግ ጥሩ በሆነ ፕላትፎርም ሊገረሰስ ይችላል፡፡
በእኛ ሀገር ጥቂት የማይባሉ ፕላትፎርሞች ቢኖሩም የመረጃ ልዉዉጡ ደካማ ስለሆነ ለማነፃፀር ስለሚያስቸግር ጥቂት ቴክኖሎጂ የደቆሳቸዉ እና ቴክኖሎጂ ያነጎሳቸዉ ዘመናዊ ዓለም ዓቀፍ የቢዝነስ ዘርፎች እና ፕላትፎርሞችን እንይ -
ፌስቡክ vs ማይ ስፔስ
በአለማችን ላይ ከ 2 ቢሊዮን በላይ ተጠቃሚ ያለዉ ትልቁ ፕላትፎርም ፌስቡክ ነዉ፡፡ በዚህ ዓለም ላይ እንደ ፌስቡክ ያህል ብዛት ተከታይ ያለዉ ሀይማኖት እንኳን የለም፡፡ ፌስቡክ ይሄንን ድል ለመቀናጀት የወሰደበት 15 ዓመታትን ብቻ ነዉ፡፡ ፌስቡክ የሚያስገባዉን ገቢ እነ ቦይንግ እና ኤይርባስ የመሳሰሉ ካምፓኒዎች እንኳን ዉድ አዉሮፕላኖችን እየሸጡ ሊያገኙት አልቻሉም፡፡ ፌስቡክ ፕላትፎርም ነዉ ፣ ብዙ ነገሮችን አንድ ጋር የሚገናኙበት ፣ እኛ ፌስቡክ ስንጠቀም ምንም የምንከፍለዉ ነገር የለም ፣ ለፌስቡክ ግን እኛ የገቢ ምንጮቹ ነን ምክንያቱም ሌሎች አካለት የእነሱን ማታወቂያዎች እንድናይላቸዉ ለፌስቡክ ስለሚከፍሉ ፤ ፌስቡክ መስራቹ ማርክ ዙከን በርግን በዓለም ካሉ ወጣቶች የመጀመሪያዉ ባለሀብት ሊዲርገዉ ችሏል፡፡
ፌስ ቡክ ምንም እንኳን ዛሬ ላይ ሀያል ቢሆንም በተጀመረበት ወቅት እንደ ማይ ሰፔስ አይነት እጀግ የገዘፉ ብዙ ተጠቃሚዎች ከነመረጃቸዉ የነበራቸዉ እና ለረጅም ጊዜ ዙፋኑን የተቆናጠጡ ካምፓኒዎችን ይበልጣል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ማይ ስፔስ የደረሰበትን የተለያዩ ጥቃቶች መቋቋም ተስኖት ተደቋቁሷል፡፡
ኔትፊሊክስ vs ዩቱዩብ vs ብሎክ በስተር
በእኔ እድሜ ያለ አብዛኛዉ ሰዉ ዴክ ፤ ከፍም ሲል ሲዲ ተከራይቶ ፊልምን ኮምኩሟል አለበለዚያም ካሴት ገዝቶ ክሩን አጠንጥኖ ሲበጠስም ቀጥሎ በቴፑ ሙዚቃን አጣጥሟል፡፡ ብሎክ በስተር በዓለም ላይ ታዋቂዉ የቪዲዮ ሲዲዎች ማከራያ ድርጅት ነበር ነገር ግን ኔትፊሊክስ የተሰኘዉ ፕላትፎርም በኢንተርኔት አማካኝነት ቪዲዮችን ማከራየት (ማሳየት) ሲጀመር ፤ ብሎክ በስተር የኔት ፊሊክስን ጡጫ መቋቋም ተስኖት ከገበያ በበቃኝ ወጥቷል፡፡ በነገራችን ላይ ብሎክ በስተር ብቻ ሳይሆን በእኛም ሀገር ያሉ አብዛኞቹ በየሰፈሩ የነበሩ የቪዲዮ አከራዮች ስራቸዉን ለማቋረጥ ተገደዋል፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት በሀገራችን እንደ ኤሌክትራ ፤ ናሆም ሪከርድስ እና ማስተር ሳዉንድ እይነት ካምፓኒዎች የሙዚቃ ገበያዉን እና ሽያጩን ተቆጣጥረዉት ነበር፡፡ ነገር ግን የዩቱዩብ መስፋፋት በተለይም በሙዚቃዉ ኢንደስትሪ እንደ ሆፕ ሚዉዚክ ፣ ምነዉ ሸዋ እና አድማስ ያሉ ገፆች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ በዚህ ጊዜ ለአንድ ሙዚቃ እስከ 1.5 ሚሊዮን በመክፈል ከፍተኛ ተዕፅኖ እያሳደሩ ይገኛሉ፡፡ ቀድመዉ ፕላትፎርሙን ስለተረዱት በዚያም እጀግ ብዙ ተመልካቾች ስላሏቸዉ ዝነኞች እና ሙዚቀኞች የእነርሱ ገፅ ጥገኛ ለመሆን ተገደዋል፡፡ ይሄም የሲዲ ሽያጭ ገበያን እጅግ አጣብቂኝ ዉስጥ አስገብቶታል፡፡
ዛሬ ላይ አብዛኞቹ በተለይም ወጣት ሙዚቀኞች የዩቱዩብ ፕላትፎርም ግንዛቤ ስላላቸዉ ስራዎቻችዉን ለሌሎች ከመሸጥ ይልቅ ለግዜዉ ከሽያጭ ብዙ ገቢ እንዲሁም እይታ ቢያሳጣቸዉም የነገን ተስፋ አድርገዉ የየራሳቸዉን የዩቱዩብ ፕላትፎርም ገፆችን መጠቀም ጀምረዋል፡፡ ከእነዚህም ዉስጥ ቴዲ አፍሮ ፣ ወንዲ ማክ ፣ አስቴር አወቀ ፣ ሳያት ደምሴ ፣ ናቲ ማን ፣ ሀመልማል አባተ እና አቡሽ ዘለቀ ይገኙበታል፡፡
አሊባባ vs አማዞን vs ኢቤይ
አለም የኦንላይን ግብይትን የሚሳልጠዉ አማዞን በዓመት ብቻ በአጠቃላይ የሚያተርፈዉ ትርፍ ኢትዮጵያ ለ110 ሚሊዮን ዜጎቿ ለአመት ከምትመድበዉ 14 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ከእጥፍ በላይ የበለጠ ነዉ፡፡ በዚህ የፕላትፎርም ዘርፍ አማዞን ብዙ ጊዜ ቢጠራም አሁን ላይ ሌላኛዉ ከኤሽያ ቻይና መቀመጫዉን ያደረገዉ አሊባባ በማይታመን ፍጥነት እየገሰገሰ ይገኛል፡፡
ለሁላችንም አርዓያ በሆነዉ የአሊባባ መስራች ጃክ ማ እና ጓደኞቹ ስለ ኢንተርኔት እንኳን በቂ ግንዛቤ ሳይኖራቸዉ የኦንላይን ግብይትን ሀሳብ ሲጠነስሱ በወቅቱ የማይነካ የሚመስለዉ ኢቤይ ጠንካራ እጆቹን በቻይና ላይ አንሰራፍቶ ነበር፡፡ ኢቤይን ሌላ ድርጅት ብልጫ ይወስድበታል ብሎ ማሰብ ከንቱነት ነበር፡፡ ይሄዉ ጊዜን ጊዜ ተካዉና የማይሆነዉ ሆነ ከተስፋ ዉጪ ምንም ያልነበረዉ አሊባባ ታላቁ ኢቤይን በዝረራ ከቻይና ገበያ ዉጪ አድርጎታል፡፡ የዛን ጊዜ ስራ አጡ ፣ ተፈላጊነት ያለነበረዉ ሰዉ ጃክ ማ ዛሬ ላይ ከአለም ቱጃር ቢሊዬነሮች አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡ ሀገራችን ለዜጎቿ ጥቅም ሲባል በኦንላይን ግብይት ለዉጪ ሀገር ካምፓኒዎች ዘግታዉ የነበረዉን በር ገርበብ ማድረጓን ተከትሎ አሊባባ እያነፈነፈ ይገኛል፡፡ በቅርቡም በሀገራችን እንደሚገባ ይጠበቃል ፣ ነገር ግን ብዙዎች የአሊባባን ጠቃሚና ጎጂ ተዕፅኖዎችን ስላልተረዳንዉ ከአንዳንድ ኢኮኖሚስቶች እና ቴክኖሎጂስቶች ዉጪ ያን ያህል ትኩረት የሰጠዉ አካል የለም፡፡ የአሊባባ መግባት ለብዙዎች በተለይም በቴክኖሎጂ ዙሪያ ላሉ እና ዘመናዊ ነጋዴዎች የስራ ዕድልን ቢፈጥርም በልማድ ለሚሰሩ ለአብዛኞቹ ነጋዴዎች ፈተና እንደሚሆን እና የመኖር ህልዉናቸዉን እንደሚፈታተናቸዉ ግልፅ ነዉ፡፡ ቻይኒቲ እስካሁን ዘረፈችን እያለን ከምናሟርተዉ ይልቅ አሊባባ ከመጣ እጅግ ብዙ የሀገሪቷን ሀብት አጥቦና ጠራርጎ ለሀገሩ ቻይና እንደሚገብር ምንም አያጠራጥርም፡፡
ቴሌግራም vs ዋትሳፕ vs ቫይቨር
ኢትዮጵያዉያን በብዛት ከሚጠቀሙባቸዉ የማህበራዊ ሚዲያዎች አንዱ ቴሌግራም ነዉ፡፡ ቴሌግራም ለአጠቃቀም ምቹ መሆኑ እና በደካማ ኢንተርኔት ዴታ በፍጥነት መስራቱ ጭምር ተመራጭ አድርገዉታል፡ ይሄ ገፅታዉም አብዛኞቻችን እንደ ቫይበር እና ዋትሳፕ ካሉ ተመሳሳይ መተግበሪያዎች እንድንርቅ እየደረገን ይገኛል ፡፡ ምንም እንኳን በዓለም ደረጃ ዋትሳፕ የተሻለ ተቀባይነት ቢኖረዉም ኢትዮጵያ ዉስጥ ግን ሙሉ በሙሉ በቴሌግራም የበላይነት ተወስዶበታል፡፡ ይሄም አልበቃ ብሎት ብዙዎችን ከፌስቡክ መንደር እያስቀረን ይገኛል፡፡ ቴሌግራም ገና ቅርብ ጊዜዉ ቢሆንም በብዙ ሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ እያግበሰበሰ ይገኛል፡፡
በነገራችን ላይ ፕላትፎርምን መስራት ብቻ ሳይሆን ፕላትፎርምን በአግባቡ መጠቀም የስኬት ሚስጢር ነዉ፡፡ ዛሬ ላይ እጅግ ብዙ ሚሊዮን ብር ከሚመደብላቸዉ እና እጅግ ብዙ ሰራተኞች ካሏቸዉ የሚዲያ ተቋማት ይልቅ በአንድ እና ሁለት ግለሰብ የሚንቀሳቀሱት ቲክቫህ ኢትዮጵያ ፤ ጌጡ ተመስገን እና ኤልያስ መሰረት ተዕፅኖ ፈጣሪ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡
ኮዳክ vs ኢንስታግራም
በእኛ እድሜ እንኳን በየፎቱ ቤቱ እየሄድን የምንነሳዉ በባለ ፊልሙ በተለይም በኮዳክ ሰራሽ የፎቶ ፊልሞች ካሜራዎች ነበር ፡፡ የተነሳነዉን ፎቶ ይበላሽ ወይንም ልክ ይሁን እንኳን የምናዉቀዉ ታጥቦ ከመጣ በኋላ ነበር፡፡ ይሄ ከትንሽ ዓመት በፊት የነበረ ድርጊት ዛሬ ላይ ነበር ሆኗል፡፡
ዛሬ ላይ የፎቶ ክንዉኑ ብቻ ሳይሆን ከዋኙ ኮዳክ በየቀኑ በሰልፊ ካሜራ የሚነሱ እና አንደ ኢንስታግራም ያሉ ፕላትፎርሞችን ያጨናነቁ ፎቶዎችን ጫና መቋቋም ስላለቻል ቁልፉን ከርችሞ ከገበያ ለመጥፋት ተገዷል፡፡ ዛሬ ከዲቂቃ በፊት የተነሳነዉ ፎቶ ወዲያዉኑ እኛ ብቻ ሳንሆን በኢንስታግራማችን ላይ የሚገኙ ሚሊዮኖች ያዪታል፡፡
ኖኪያ vs ሳምሰንግ vs ሁዋዊ
ስኔክ ጌም የተጫዉትንባቸዉ ፣ ወድቀዉ ንክች የማይሉት ፣ በ2ጂ ኔቶርክ የተነጋገርንባቸዉ የኖኪያ ስልኮች የቅርብ ጊዜ ትዉስታዎቻችና ናቸዉ፡፡ የፊንላንዱ ኖኪያ የአንድሮይድ ኦፕሮቲንግ ሲስተም ሲመጣ ከመቀበል ይልቅ የራሱን ለመስራት ጉድጉድ ማለት ቢጀምርም ከስኬት ይልቅ ወደ ዉድቀት ጉድጓድ ዉስጥ ራሱን በመክተቱ ከገበያ ከራቀ ሰነባብቷል ፤ ንግስናዉንም ለሳምሰንግ አስረክቧል፡፡ አሁን ላይ ኖኪያ ከስህተቱ ተምሮ የተሻሉ ስልኮችን ለገበያ በማቅረብ የነበረ ስሙን ለመመለስ እየተጋ ነዉ፡፡
ነገ ምን እንደሚፈጠር አይታወቅም ፤ አንድሮይድን ይጠቀም የነበረዉ ሁዋዌ እንዳይጠቀም በተጣለበት እገዳ ምክንያት በሚያስገርም ሁኔታ እጅግ ጥሩ የራሱን መተግበሪያ አዘጋጅቶ ለገበያ አቅርቧል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ጎግል ፉቺሳ የተባለ ኦፕሬቲንግ ሲስተም እያዘጋጀ ሲገኝ ለዚያም እንዲረዳዉ ፍለተር የተባለ ሞባይል መተግበሪያ ማዘጋጃ ለጥቅም አዉሏል ፡፡ ጦርነቱ እና ሀያልነቱ በፕላትፎርም ነዉ ምክንያቱም የወደፊቷ ዓለም ሙሉ ለሙሉ የፕላትፎርም ዓለም ናትና፡፡ የነገ ተዕፅኖ ፈጣሪ ዛሬ ላይ ገንዘብ ያለዉ ሳይሆን ዛሬ ላይ ፕላትፎርም ያለዉ እና መረጃን ያከማቸ ሰዉ ነዉ፡፡
ኢክሳይት vs ጎግል
ከዓመታት በፊት አክሳይት ዶት ኮም ልክ እንደ ዛሬዉ ጎግል ስሙ የገዘፈ የመረጃ መፈለጊያ ቦታ ነበር፡፡ የዛሬዉ ጉግል ባለቤቶችም የሰሩት ፈጠራ የኤክሳይት ባለቤቶች እንዲገዟቸዉ ብዙ ጊዜ ተማፅነዋቸዉ ነበር፡፡ የዛን ጊዜ ጎግል እንዲሸጥበት ለኤክሳይት የቀረበዉ እዚህም ግባ የማይባል በጣም ትንሽ ብር ነበረ፡፡ ነገር ግን ጊዜን ጊዜ ወለደዉና የዛን ጊዜ ጎግልን የናቀዉ ኤክሳይት የናቁት ያዋርዳል ነዉ እና በጎግል ከገበያ ወጪ ሆኖ ከህይወት ወደ ሞት ጫፍ ተሸጋግሯል፡፡
ሁላችንም የጎግል ጥገኛ ሆነናል፡፡ ኑሮ ያለ ጎግል የማይታሰብ እየሆነ መጥቷል ፡፡ ከግል መረጃችን እስከ የትኛዉም የዓለም መረጃ የምናገላብጥበት እና የምንፈልግበት መሳሪያችን ጎግል ነዉ፡፡
ኤች ፒ vs ሊኖቮ vs ቶሺባ
አንድ ቢዝነስ ሲፈካ ሌላዉ ጫናዉን መቋቋም ያልቻል እየጠወለገ መምጣቱ አይቀሬ ነዉ፡፡ አንዴ ክንፋቸዉን የተመቱ ቢዝነሶች ደግሞ የመመለሳቸዉ ነገር የማይመስል ነዉ፡፡ ሁላችንም እየተጠቀምንበት የምንገኘዉ ቶሺባ ኮምፒዉተር አንዱ ነዉ፡፡ ቶሺባ ዛሬ እንጠቀምበት እንጂ ነገ ከነገወዲያ ቅርስ ሆኖ የመምጣቱ ነገር እዉን እየሆነ መጥቷል፡፡ ምክንያቱም በባንክ እዳ እና ተያያዝ ጉዳዮች ቶሺባ ኪሳራ ዉስጥ ከገባ ሰነባብቷል፡፡ እንደ ሌኖቮ እና ኤችፒ ያሉ ካምፓኒቺዎች ደግሞ በተቃራኒዉ በገበያዉ ዉስጥ ድርሻቸዉ የበለጠ እያሻቀበ ፤ ትርፋማነታቸዉ እየተመነደገ ይገኛል፡፡
ጂሜይል -- ያሁ
ከጥቂት ዓመታት በፊት በእኛም ሆነ በሌላዉ ሀገር ኢሜይል ሲባል ጭንቅላታችን ዉስጥ የሚመጣዉ ያሁ ነበረ፡፡ ያሁ በደረሰበት ተደጋጋሚ የሳይበር ጥቃት በቢሊዪን የሚቆጠሩ ደንበኞቹን መረጃ ተመዝብሮ ታላቅነቱንም ለተረኛዉ ጂሜይል ለማስረከብ ተገዷል፡፡ በዚህ ጊዜ ጂሜይል የሚሰጠዉ የማጠራቀሚያ ቦታ እስከ 15 ጊጋ ባይት ብቻ ሲሆን በተቃራኒዉ ያሁ ግን በብዙ እጥፍ እስከ 1000 ጊጋ ባይት ወይንም 1 ቴራ ባይት ይሰጣል፡፡ ነገር ግን ያሁ ይሄን ያህል አድርጎ እንኳን ደንበኞችን ሊያስቀር እና የጂሜይልን ጫና ሊቋቋም አልቻለም፡፡ ጂሜይል በዓለማችን ትልቁ የኢሜይል መረጃ መለዋወጫ ሆኖ ህይወታችንን ቀላል እያደረግልን ይገኛል፡፡
በ2019 የፎርብስ መፅሄት በሚያሳዉቀዉ የአለም የቱጃሮች ሰንጠረዝ መሰረት ካሉት ባለሀብቶች መጀመሪያ ላይ የሚገኙት ባሀብቶች የገቢ ምንጫቸዉ ፕላትፎርም እና ፕላትፎርም ነዉ፡
1. ጆሴፍ ቤዞስ - ከ110 ቢሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር ከአማዞን
2. ቢል ጌት - 95.6 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከማይክሮሶፍት
5. ካርሎስ ስሊም - 64 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከቴሌኮም ኢንደስትሪ
7. ላሪ ኢሊሰን - 63 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከኦራክል
8. ማርክ ዙከንበርግ - 62.3 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከፌስቡክ
9. ሚካኤል ብሎምበርግ - 55.5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከብሎምበርግ
10. ላሪ ፔጅ - 50.8 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከጎግል
የፕላትፎርም ቢዝነሶች በኢትዮጵያ ላይ ቢስፋፉ በ 2 ምክንያቶች ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጭምር የተሻለ ገቢ የሚያስገኝ ይሆናል የመጀመሪያዉ ምክንያት ሀገሪቷ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣት የስልክ ተጠቃሚዎች ሲኖሯት ሁለተኛዉ ደግሞ ገና ያልዳበረ ኢንደስትሪ ስለሆነ ከባድ የቢዝነስ ፉክክር የለዉም፡፡ ለዚያም ይመስላል እንደ አሊባባ ፤ ሳፋሪ እና ቮዳፎን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ተቋማት ገበያዉን ለመቀራመት አይናቸዉን የሚያማትሩት፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ከመግባታቸዉ በፊት ነገሩ በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት እንዳይሆን የሀገራችንን ስታርት አፖች እና የቴክኖሎጂ ካምፓኒዎችን ማበረታታት ይገባናል፡፡
ለዛሬዉ በዚህ ይበቃኛል ምናልባት ወደፊት ደግሞ በሀገራችን ስላሉት እና ተስፋ ስለጣልንባቸዉ የፕላትፎርም ዉጤቶች እናወጋለን፡፡ ሠናይ ዘመነ ፕላትፎርም ይሁንልን …
Post Comment