ሚስጥረ ስኬት
አንተ እኔ አንቺ ስኬታማነትን እያለምን ፣ የስኬታማነት መንገዶች እየተሰወሩብን ፣ አንዳንዴም በእድለኝነት እያሳበብን ፣ ስኬታማነት ሲቀናን ቀመስ እያደረግንዉ ሳይቀናን ደግሞ እያለምነዉ በሀሳብ ጎዳና ላይ እንገኛለን፡፡ ብዙ ሰዎች እንደሚስማሙበት ስኬታማነታችን የሚወሰነዉ በገንዘባችን እና በእዉቀታችን ሳይሆን በአሸናፊነት አስተሳሰባችን እና በማይበገር ስነ-ልቦናችን ነዉ፡፡ እስኪ በዚህ ፅሁፍ ዉስጥ ከተመከርኩት ፣ ከተዘከርኩት ፣ ከቃረምኩት እና ከቀሰምኩት የስኬትን ሚስጥር ሹክ ልበልህ/ሽ፡፡
ለማሰብ የሚከብድ አቅም ተሸክመህ እንደምትጓዝ ታዉቃለህ ? ካወቅክ አቅምህ እንቅልፍህን ይነሳሀል ፤ አላማህን አንድታሳካ ቀን ከሌት ያተጋሀል ፤ ሁሉንም ነገር ማሳካት ትችላለህ፡፡ አንድ የሚከብድህ ነገር ቢኖር ሁሉንም ማስደሰት መቻል ነዉ እሱን እንዳትሞክረዉ አትችለዉምና :: እንኳን የአንተ ስራ የፈጣሪ ቅንነት እና በጎ ስራ ሁሉንም አያስደስትም እና ፤ ያንተ ማደግ የሚያስደስታቸዉ እንዳሉ የሚቀነቅናቸዉም እንዳሉ ተረዳ ፤ ሁሉንም ለማስደሰት መሞከር የሽንፈትህ መጀመሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ እምነት እና ፅናት ካለህ ድል ሁሌም ያንተ ናት ታዉቃለህ አይደል ያ ትንሽ ልጅ ዳዊት ያንን ግድንግድ እና ግዙፍ ጎልያድን በአንድ ጠጠር እንደረታዉ፡፡ የአንተም የዉስጥ አቅም እንደዚህ ነዉ ብዙዎችን መርታት እና መማረክ ትችላለህ ሚስጢሩ ያለህን አቅም መረዳቱ ላይ ነዉ፡፡ አንተ ያለህ አቅም ከተጠቀምክበት ትንታግ የሆነ ሀይል አለህ ፤ ካንተ አልፎ አለምን መቀየር የሚያስችል፡፡ ልብ በል ይቺ ዓለም የተቀየረችዉ በጣም ጥቂት በሆኑ ደመ ሞቃት ትንታጎች ነዉ፡፡ ሌላዉ አብዛኛዉ ማህበረሰብ አጃቢ እና ጊዜዉ ሲደርስ ወደማይቀርበት ዓለም ተመልሶ ሂያጅ ነዉ፡፡ አቅማቸዉን ቀድመዉ የተረዱ ስኬታማዎች ብቻ ናቸዉ ላይሞቱ ለዘላለም የሚኖሩት፡፡
ቅን ሁኚ ቅን ለመሆን ምንም መስፈርት አይስፈልገዉም ፤ ቅንነትሽን ለሰዉ ለማሳየት ብለሽ እንዳታረጊዉ ፡፡ ይቺ ዓለም በብዙ አሀዞች የሚቆጠሩ አመታትን ኖራለች ፤ ብዙዎችን ተቀብላ ብዙዎችን ሸኝታለች ፤ ከእነዚሀ የትየለሌ አመታት ዉስጥ ያንቺ ድርሻ በአማካኝ 60 አመት ነዉ፡፡ ይቺን ኢምንት የሆነች የህይወት ቆይታሽን በቅንነት እና ከልብ በመነጨ ደስታ ብታሳልፊያት ነፍስሽ ምን ያህል ሀሴት የተሞላች ስኬታማ ነፍስ ትሆናለች፡፡ በፈጣሪሽም ዘንድ የከበረ ቦታ ያስገኝልሻል፡፡ አንድ አባባል ታክሲ ላይ አንብቤ ነበር ለሰዉ ቅን እንጂ ቅንቅን አትሁን ይላል፡፡ እዉነት ነዉ በህይወትሽ ከትንሽ እስከ ትልቅ ነገር ለሁሉም ቅን ሁኚ ያን ጊዜ አንቺነትሽ ለዘላለም በሰዎች ዘንድ ታትሞ ይኖራል፡፡ አንቺነትሽን ሞት አይንደዉም ስምሽ ከመቃብር በላይ ገንኖ ይወጣል፡፡ አንቺ ቅን ሆንሽ ማለት ብዙ ወጪ ሳታወጪ ብዙ ትርፍ አገኘሽ ማለት ነዉ፡፡ ቅን ያደረግሽላቸዉ ሰዎች ለአንቺ በምንም አይነት ክፍያ ልታገኚዉ የማትችይዉን በልባቸዉ ዉስጥ የሚገኝ የይዞታ ካርታ በቁጥጥርሽ ስር አዋልሽ ማለት ነዉ ለራስሽ ደግሞ በየትኛዉም ገበያ ላይ አሳደሽ የማትገዢዉን ዉድ ዉስጣዊ ደስታ በርካሽ አገኘሽ ማለት ነዉ፡፡
አላማ እና መድረሻ ይኑርህ ፤ መድረሻህ ካላወቅህ ግን ሁሉም መንገዶች ወደተለያየ አቅጣጫ ይወስዱሀል ፤ አንዳንዶችቹም ከገደል ጫፍ ላይ ያደርሱሀልና፡፡ ህልም እና ራዕይ ካለህ ደግሞ ሁሉም እንደተጓዘዉ መጓዝ አይጠበቅብህም ምክንያቱም የአንተ መንገድ እንደ መንጋዉ ሳይሆን የተለየ እና እጅግ ስኬታማ ነዉ፡፡ ታዉቃለህ አይደል 99 በመቶ የአለም ህዝብ በትንሾቹ 1 በመቶ የሚሆኑት እንደሚመራ እነሱ የተለዩ ሰዎች ሆነዉ አይደለም ፡፡ ነገር ግን ነገሮችን የሚያዩበት እና የሚጓዙበት መንገድ እጅግ የተለየ ነዉ፡፡ ስኬታማ ሰዎችም የተለዩ ነገሮችን የሚሰሩ ሳይሆኑ ነገሮችን በተለየ መንገድ የሚሰሩት መሆናቸዉን ልብ ልትል ይገባል፡፡ አላማ ካለህ ፤ የፅናትን አክሊል ከደፋህ ከፊት ለፊትህ የሚገጥም ጋሬጣ ሁሉ እዳዉ ገብስ ነዉ፡፡ አንተን ሳያከስምህ አንተ ታከስመዋለህ ፡፡ አላማህን ካወቅህ መድረሻህን ታዉቃለህ ፤ መድረሻህ ካወቅህ ደግሞ ዛሬ ያልጠረግከዉ መንገድ ለነገ ከየትም ስለማይመጣ መንገድህን አሁኑኑ መጥረግ ትጀምራለህ፡፡
መልካም አስቢ ፤ አመለካከከትሽ የሚወሰነዉ በምርጫሽ ነዉ ፡፡ አንድን ሰዉ ከወደድሽዉ አእምሮሽ ከእሱ ከሚወጡ ቃላቶች ጥሩ ጥሩዎቹን ይወስዳል ሰዉየን ከጠላሽዉ ደግሞ ምን ቁም ነገር ቢያወራ አእምሮሽ መጥፎ መጥፎዉን ይነቅሳል፡፡ ነገሮችን በቀና መልኩ መተርጎም እንደሚቻለዉ በአሉታዊ ጎናቸዉ ማየትም ይቻላል ፤ ይህ የሚወሰነዉ ለአእምሮሽ በምትሰጪዉ መልዕክት ነዉ፡፡ አዕምሮሽ የአንቺ ሎሌ ነዉ ፤ አንቺ የመገብሽዉን እና ያወረስሽዉን ብቻና ብቻ ነዉ ህሊናሽ ይዞ የሚቆየዉ፡፡ መልካም ማሰብ የሚገርም አእምሮአዊ ብቻ ሳይሆን አካለዊም ለዉጥ አለዉ ፡፡ ብዙ ግዜ የታማሚዎች ጤንነት ከአስተሳሰብ ጋር ይያያዛል፡፡ እድናለሁ የሚል ቀና ተስፋ ያለዉ ታማሚ ቶሎ የመዳን እድሉ የሰፋ ሲሆን ሞትን የሚያስብ ደግሞ ያዉ የመዳን እድሉ ይቀነሳል ምክንያቱም የአእምሮአችን ተግባር የአስተሳሰባችን ነፀብራቅ ነዉና፡፡ መልካም ካሰብሽ በቁምሽ አትሞቺም ፤ ስኬታማነትሽ በመልካምነትሽ ታጅቦ አንድ ቀን መምጣቱ አይቀርምና፡፡
ድክመትህን ለመስማት ፈቃደኛ ሁን ፤ እዉነተኛ ድክመቶችህን ሊነግሩ ለመጡ ወዳጆችህ ጆሮህን ስጣቸዉ ምስጋናም ቸራቸዉ ፤ ምክንያቱም የእነሱ ምክር እና ተግሳፅ ነዉ ለአንተ አርማታ ሆኖ ሙሉ ሰዉ እንድትሆን እና ቆመህ እንድትሄድ የሚያደርግህ ፡፡ እንደዚህ ስል ደግሞ ለእነዚያ ሀሜተኞች ጆሮ ስጣቸዉ እያልኩህ አይደለም ፤ ሀሜት አንድ ደስ የሚል ገፅታ አለዉ እሱም ዉጪ ዉጪዉን እንጂ አንተ ጋር አይመጣም ስለዚህ ትኩረት ንፈገዉ፡፡ ራስህን የምትፈትሽ ከሆንክ ለሽንፈት አትዳረግም ፤ አንተ የሂወትህ ሾፌር ነህ የሚያስፈልግህን ነዳጅ እና ጎማ በበቂ ሁኔታ መያዘህን ካረጋገጥክ ጉዞዉ አያሳስብህም ፤ ጎማህ በቂ አየር የለዉም ስለዚህ አስነፋዉ የሚልህ ጓደኛ ካገኘህ ጎማዉን ከእንደገና አረጋግጠህ በቂ አየር ከሌለዉ ለአስተያየቱ አመስግነህ ጎማህን አየር አስሞልተህ ትጓዛለህ ፤ ጎማዉ በቂ አየር ካለዉ ደግሞ ጓደኛዬ ተሳስቶ ነበር ብለህ መንገድህን ትቀጥላለህ፡፡ አለበለዚያ የጓደኛህን ምክር ካልሰማህ እና ራስህን ካልፈተሸክ ግን መጥፎ ቦታ ላይ ትቆምና መመለሻ አጥተህ እንደወጣህ ትቀራለህ፡፡ ችግርህን ተቀባይ ልትሆን ይገባል ፤ የእናቴ ቀሚስ አወላከፈኝ አታብዛ ፡፡ አንተ ግን የእናቴ ቀሚስ አወላክፎኝ ሳይሆን መዝለል አቅቶኝ ነዉ የወደቅኩት ካልክ ራስህን ታዉቃለህ ማለት ነዉ፡፡ ሀላፊነትን መሸከም ስትችል ነዉ ስኬታማ እና የማይበገር የምትሆነዉ አለበለዚያ የራስክን እከክ ለሌላዉ ስታሸጋግር መፍትሄ አልባ የሆነ ኑሮ መኖርህ አይቀሬ ነዉ፡፡ ግሬድ A ስታገኝ ጎጆ ሰራሁ F ስታገኝ ደግሞ እከሌ ጫረኝ ካልክ ለመለወጥ እና ድክመትህን ለመለየት ፈቃደኛ አይደለህም ማለት ነዉ፡፡ ለምትሰራቸዉ እያንዳንዶቹ እንቅስቃሴዎች ካጠፋህ በበላይነት ተጠያቂዉ አንተዉ ፤ ጥሩ ከሰራህም ተወዳሹ አንተዉ ልትሆን ይገባል፡፡
እዉቀትን ብቻዉን መልቀሙን ትተሸ ከጥበብ ጋር ሰብስቢ ፤ እዉቀት ያለ ጥበብ እና ተግባር ከንቱ ነዉ፡፡ ብዙ መፅሀፍ ማንበቡ ፣ ቅኔ መቃኘቱ ፣ ክራር መደርደሩ ፣ ድግሪ በድግሪ ላይ መደራረቡ ስኬታማ አያደርግሽም ምክንያቱም ማንም ሊከዉነዉ የሚችለዉ ነገር ነዉና የሰራሽዉ፡፡ ከላይ ያሉትን ነገሮች ተጠቅመሸ ግን ያንቺን ዉስጠት እዉን ካደረግሽ እና ጥበበኝነትሽን እዉን ካደረግሽ አሁን ስኬታማ ነሽ፡፡ መቋጠሪያ ጆንያ ዉስጡ ካልተሞላ መቆም እንደማይችለዉ ሁሉ አንቺም ስኬትን ሳታስቢዉ ብታገኚ እንኳን እዉቀትን እና ጥበብን ዉስጥሽን ካልሞላሽዉ እንደ ባዶ ጆንያ መቆም ይሳንሻል፡፡ ስኬቱም አንቺን ለቆ ሞልቶ ወደ ሚጠብቀዉ ተረኛ ስኬታማ ይነጉዳል፡፡ እዉቀት ያለ ጥበብ እና ትምህርት ያለ ተግባር አንድ አይነት ናቸዉ፡፡ ሁለቱም አእምሮን ከመሙላት እና ራስን ጠቅሞ ከማኖር ያለፈ ለሌሎች አይተርፉምና፡፡
ዉድቀትን አትጥላ ፤ ዉድቀት የስኬት መንደርደሪያ መሆኑን ልትረዳ ይገባል ፤ ማንኛዉም የስኬት ጫፍ ላይ የተቆናጠጠ ሰዉ ጠጋ ብለህ ብታወጋዉ ያለፋቸዉን ፈታኝ ችግሮች እና ያጋጠሙትን አሜኬላዎች ያስወገደበትን ሚስጥር ሹክ ይልህል ፡፡ አየህ ወርቅ ወርቅ ለመሆን በእሳት ሊፈተን ግድ ይለዋል አለበለዚያ ወርቅ መሆን እንዳማረዉ ይቀራል እንጂ ከሌሎች ድንጋዮች የተሻለ አይሆንም፡፡ አንተም ችግሮች ሲገጥሙህ የምትወስዳቸዉ እና የምታልፍባቸዉ መንገዶች ናቸዉ ስኬታማም ፣ ተሸናፊም የሚያደርጉህ፡፡ ዉድቀት እንዳይመጣ የምትፀልይ ከሆነ አንተ ቀድመህ እጂህን ለዉድቀት ካቴና አስረክበሀል እግርህንም በዉድቀት እግረ ሙቅ ተይዟል ማለት ነዉ፡፡ መዶሻ ብረትን ቀጥቅጦ ቅርፅ ሲያሲዘዉ መስተዋትን ግን አድቅቆ ይሰባብረዋል፡፡ አንተም የምትፈተንበትን መዶሻ ተቋቁመህ ዉድቀትን ድል ካደረክ ስኬታማ ትሆናለህ፡፡ እንደ መስተዋቱ ተሰባብረህ ተስፋ ከቆረጥክ እዚያዉ ከስመህ ስኬትን ስትመኝ ትኖራለህ፡፡
እድሎችሽን ተጠቀሚ ፤ ብዙዎች በእድል እና በጥረት መካከል ከፍተኛ ክርክር ያነሳሉ ፡፡ እድል ከጥረት የተሻለ ነዉ አይ ጥረት ያለ እድል ከንቱ ነዉ ይላሉ ፡፡ አሸናፊ የሚያደርግሽ እድል ብቻዉን ሳይሆን እድሎችን እንዴት ተጠቅመሻል የሚለዉ ነዉ፡፡ አንቺ ሎተሪ ደረሰሽ ቢባል ፤ አንቺ እድለኛ ሳትሆኚ እድልሽን የተጠቀምሽ ነሽና ምክንያቱም እኔም ሎተሪዉን ለመቁረጥ እና እድሌን ለመጠቀም ስላለሞከርኩኝ፡፡ በሂወትሽ ላይ የሚመጣ እድል በአግባቡ ከተጠቀምሺዉ አንቺ ስኬታማ ትሆኛለሽ ብዙዎቻችን እድሎች ወደ እኛ ሲመጡ አናዉቃቸዉም አንዳንዴ ምናልባት ካለፉ በኋላ ሊገለፁልን ይችላሉ፡፡ ስኬታማ ሰዎች ግን እድሎችን አነፍንፈዉ የተጠቀሙት እንደሆኑ ልብ ልትይ ይገባል፡፡ ንቅ ሁኚ እድል የት እንዳለች አታዉቂም ፤ እዚህ የምታነቢዉ ፅሁፍ ጋር ልትሆን ትችላለች አለበለዚያም ታክሲ ላይ ስትጓዢ እና ዙሪያሽን በደንብ ቃኚ፡፡ የእድል ትልቅ እና ትንሽ የለዉም ፤ ምክንያቱም ትንሽ እድል ወደ ትልቅ ጎዳና ታደርሰናለችና፡፡ እያንዳንዶቿን እድሎችሽ አንጠፍጥፈሽ ተጠቀሚያቸዉ፡፡
ተግባሪ እንጂ ተናጋሪ አትሁን ፤ የአብዛኞቻችን ችግር አንደበታችን እና አስተሳሰባችን ፍየል ወዲያ ቅዝምዝ ወዲህ ሆኖ ነዉ የተቸገርንዉ፡፡ ህይወታችንን እንኖረዋለን ወይስ እሱ ይኖርብናል ፡፡ ቃል አባይ የሆነን ሰዉ ማንም አይወደዉም ፤ ማህበረሰባችን ያሉት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ ይላል ይሄም ምን ያህል ለቃሉ እምነት እንዳለዉ ያስረዳሀል፡፡ ድርጊቶችህ ከቃላት የበለጠ መናገር እና ማስተጋባት ይችላሉ ፤ ስለዚህ አንተነትህን እና ማንነትህን አንተ ሳትሆን ተግባሮችህ እንዲናገሩልህ ፍቀድላቸዉ፡፡ አንድ ሰባኪ ስለ አብርሀም ሲደሰኩር ዉሎ ተግባሩ ግን የቃየል ከሆነ ለሌሎች ብርሀን እየገለጠ እሱ ግን በጨለማ ዉስጥ እየኖረ ነዉ፡፡ የሚፀድቀዉ ደግሞ ያወራዉና የሰበከዉ ሳይሆን የኖረዉ እና የኖረዉ ብቻ ነዉ፡፡ ስለዚህ በቃ ሰርተህ አሳይ እንጂ በቃላት አትሸንግል አለቀ፡፡
የሚጠቅምሽን ብቻ መርጠሽ ስሚ ፤ መርጠሸ አዉሪ ፤ አንዳንዴ ጭንቅላታችን በፈጣሪ ሲሰራ ድንቅ ተደርጎ ነዉ የተሰራዉ ብየ አስባለሁ ፤ የሰማንዉን ሁሉ እንደ ካሴት የምንቀዳ ቢሆን ኖሮ የጭንቅላታችን ቦታ ሞልቶ አሁን ለማሰብ አንኳን የምትተርፍ ቦታ ማግኘት ከባድ ይሆን ነበር ፤ የትላንቱን ጥላሸት መርሳት ተስኖን ዛሬ መኖር ይከብደን ነበር፡፡ አምላክ መለኛ ነዉ እና መርሳት የሚባል ትልቅ ጥበብ አደለን፡፡ ቡና ላይ ቁጭ ብለሽ ጎረቤትሽን አትቦጭቂ መጀመሪያ የራስሽን ቀዳዳዎች ለመሸፈን እና ጥሩ ሰዉ ለመሆን ሞክሪ፡፡ ጆሮሽም ማጥለያ ሊኖረዉ ይገባል ፤ ካልጠቀመሽ አትስሚዉ ፡፡ ስትናገሪም ለከት ይኑርሽ ከአንደበትሽ የወጣ መጥፎን ቃል በምንም አይነት መንገድ መመለስ አትችይም፡፡ ለጥሩ ሰዎች ብቻ አንደበትሽን እና ጆሮሽን ለግሻቸዉ ያን ጊዜ አንደበትሽም መልካም ያወጣል ጆሮሽም መልካም መልካሙን መርጦ ይሰማል፡፡
አሜን ባይ አትሁን ፤ ሰዉ ስላደረገ ብቻ የምታደርግ ከሆነ በተሳሳተ እይታ ዉስጥ ነህ ማለት ነዉ፡፡ ለአንተ የማይስማማህ ከሆነ መሞገት እና አለመቀበል ይኖርብሀል፡፡ አለበለዚያ ያመጡልህን ሁሉ አሜን እያልክ የምትቀበል ከሆነ ማንም እየመጣ የፈለገዉን እዳ አንተ ላይ እያራገፈብህ ቆይቶ ራስህን ስትፈልገዉ ታጣዋለህ፡፡ ለምን ባይ ከሆንክ ግን የምትፈልገዉን ብቻ እየመረጥክ ነዉ ማለት ነዉ፡፡ ግትር ሳይሆን ፈታኝ ልትሆን ይገባል ፤ ያን ጊዜ ሰዎች አንተነትህን ይቀምሱታል፡፡ ሰዉ ቃሪያ የሚበላዉ እኮ የሚያቃጥል ስለሆነ እኮ ነዉ ፤ ጨዉ ጨዉ የሆነዉ በጨዋማነቱ ነዉ ፤ ሎሚ ሎሚነቱ የሚታወቀዉ ስለሚኮማጠጥ ነዉ ፤ ኮሶ በሽታን የሚነቅለዉ እጅግ መራር ስለሆነ እኮ ነዉ ፤ አንተም ፈታኝ እና አመዛዛኝ ከሆንክ እሙን ነዉ ፈተናዎችህ ይከብዳሉ ፤ ብዙዎች አይረዱህም ነገር ግን እመነኝ አሸናፊነት ግን ያንተ ነዉ፡፡ የጓደኞችህ ጫና የአንተን ህይወት ሊቀይረዉ አይገባም ፤ ከባድ ፈተናዎችን አልፈህ አንተነትህን ልታሳያቸዉ ይገባል፡፡
በራስሽ ተማመኚ ፤ ለራስሽ ክብር ስጪ እና ተማመኚበት፡፡ አንቺ ያልተማመንሽበት እና ያልተቀበልሺዉን ማንነትን ሌላ ማንም ሊተማመንበትና ሊቀበለዉ አይችልምና፡፡ አሸናፊዎች እና ሰኬታማዎች በራሳቸዉ ይተማመናሉ፤ ነገሮችን ሁሉ በጥረታቸዉ ድል አንደሚያደርጉ ያምናሉ፡፡ ለእያንዳንዷ ድርጊታቸዉ ምክንያታዊነትንና ሀላፊነት መዉሰድን የያዘ ስለሆነ የሚመጣዉን ለመቀበል ራሳቸዉን አሳልፈዉ ይሰጣሉ፡፡ የአንቺ በራስ መተማመን ከአንቺ አልፎ ለሌሎች ተስፋ እና ብርሀንን ይፈነጥቃል ፤ ሰዎች እምነት እንዲጥሉብሽ ያደርጋል ፤ ይህ ከሆነ ደግሞ የስኬታማነትሽ ነገር ከጊዜ ወደ ጊዜ ወዳለሽበት አይኑን አፍጥጦ እንዲመጣ ያደርገዋል፡፡
ጊዜ አጠቃቀምህ የአንተን ሂወት ከሚወስኑ ነገሮች እጅግ ጠቃሚዉ ነዉ፡፡ ለተረዳዉ ዓለማዊ ንጉስ ገንዘብ እና ንዋይ ሳይሆን ዓለማዊ ንጉስ ጊዜ ነዉ፡፡ ህፃናትን አዋቂ ፤ ድሀን ሀብታም ፤ ተመፅዋችን መፅዋች ፤ ምዕመንን ካህን ፤ ተማሪን መምህር ፤ ወታደርን ሀገር መሪ ማድረግ የሚቻለዉ ቢኖር ጊዜ እና ጊዜ ብቻ ነዉ፡፡ ጊዜን ተጠቅሞ ባህሩን የተሻገረ የስኬትን ደሴት ሲቆናጠጥ ፤ ጊዜዉን ያልተጠቀመ ገና ከጊዜ ደሴት ሳይደርስ ረጅሙ ባህሩ ዉጦ ያስቀረዋል፡፡ ስለዚህ የአንተም ምርጫ ጊዜን ተጠቅመህ ከስኬት ደጃፍ መድረስ አለበለዚያም በባህሩ ሰምጠህ በዚያዉ መቅረት ነዉ፡፡ ከስኬት ደጃፍ መድረስ ከሆነ ፍላጎትህ ከአሁን ጀምሮ ለጊዜህ ክብር ስጥ እና አንግሰዉ ፤ ለነገ ማሳደሩን ትተህ የዛሬን ዛሬ ላይ ጨርሰዉ ፤ የነገን ደግሞ ነገ ላይ ትከዉነዋለህና፡፡
ጓደኛችሽን ንገሪኝና ማንነትሽን እነግርሻለሁ ነዉና አባባሉ የጓደኞችሽ አስተሳሰብ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ያንቺ አስተሳሰብ ላይ ተዕፅኖ ያሳድራል፡፡ ይቺን አለም ለብቻ መግፋት ተራራን ገፍቶ እንደማንቀሳቀስ እጅግ ከባድ ነዉ ፤ ስለዚህም አብረዉሽ የሚያዘግሙ ጓደኞች ያስፈልጉሻል፡፡ ጓደኞችሽ ግን አብረዉሽ ሲያዘግሙ ወደፊት እንጂ ወደኋላ የሚስቡሽ ሊሆኑ አይገባም፡፡ ወደኋላ የሚጎትትሽ ጓደኛ ካለ በመንገድሽ ላይ የቆመ ጋሬጣ ነዉና ከመራመድሽ በፊት መንጥሪዉ ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ከኋላ ከኋላ እየተከተለ እየወጋሽ ከስኬታማነት ጎዳና በገዛ ፈቃድሽ ያስወጣሻል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት አብዛኞቹን የምትተገብር/ሪ ከሆነ እርግጠኛ ሆኜ ልንገርህ /ሽ ስኬት ያንተ/ቺ ናት ማንም ከዙፋንህ/ሽ ንቅንቅ አያደርግህም/ሽም አሸናፊነት እና ድል ያንተ እና ያንቺ ነዉ ምክንያቱም ጦርነቱ የጭንቅላት ጥበብ ጦርነት ነዉና፡፡
Post Comment