መክሊት


መክሊት

          ፌስቡክ ላይ እየተጠቀምኩኝ ሳለሁ አንድ ፈገግም ፣ ፈልሰፍም ያደረገኝን የሚከተለዉን ፎቶ ተመለከትኩኝ:: እንደ እኔ እይታ ይህ ፎቶ ቀልድን ብቻ ሳይሆን በዉስጡ ብዙ ነገሮችን አቅፎ ይዟል ፡፡ እስከመቼ ስራ ፈልገን ? 17 ዓመታት በትምህርት ዓለም ላይ ያጠፋ ሰዉ ስራ አጥቶ ኮብልስቶን ለማንጠፍ ሲሯሯጥ ማየት የተለመደ ነዉ ፤ ኮብልስቶን ማንጠፍ ዝቅተኛ ስራ ነዉ እያልኩ አይደለም ግን ያ ሰዉ 17 ዓመት የደከመበት ነገር ፍሬ ቢስ መሆኑ እና ለሰዉዬዉ የሞራል ዉድቀት ለሀገሪቷ ደግሞ ክስረት መሆኑ ነዉ የሚያስቆጨዉ ፡፡ይህ የስራ መጥፋት የተለያዩ መንስኤዎች አሉት ፡፡ ከነዚያም ዉስጥ መክሊትን አለማወቅ ፤ ዓላማ-ቢስ መሆን ፤ ደካማ የስራ ባህል እና የስራ ፈጠራ አለመኖር ዋና ዋናዎቹ ናቸዉ ፡፡

          ጥለፈኝ የሚል ፊልም ላይ የማስታዉሰዉ አንድ አብርሀም የሚባል ገፀ ባህሪ የሚናገራት እና የምወድለት አንድ አባባል አለች ፤ እንደዚህ ትላለች “የሰዉ ልጅ የመጀመሪያ ስህተቱ መክሊቱን አለማወቁ ነዉ ፤ ጥሩ ግንበኛ መሆን እየቻለ ዶክተር ካልሆንኩ ፤ ጥሩ ፖሊስ መሆን እየቻለ ፓይለት ካልሆንኩ ፤ ጥሩ ነጋዴ መሆን እየቻለ ዘፋኝ ካለሆንኩ እያለ ስንቱ ነዉ ላልተፈጠረለት ዓላማ እየኖረ ሳይሳካለት የሰዉ ሸክም ሆኖ የሚሞተዉ ” ትላለች፡፡ ቤት ይቁጠረዉ ስንቶቻችን ነን የምንኖርበት ዓለማ እና መነሻ መድረሻችንን የምናዉቀዉ ? ኢንጅነሮች መሆን እየፈለግን ለእናት አባታችን ብለን ዶክተሮች የሆንነዉ ፤ ስንቶቻችንስ ነን ጥሩ ኢንጅነሮች መሆንን እየቻልን ሰዉ ሲገባ ስላየን ብቻ ዶክተር ካልሆንን ብለን ያለ መክሊታችን የተሰነቀርንዉ ፤ የሰዉ ልጅ ምንም እንኳን የሆነ ነገር ላይ ቢሰማራም የተሰማራበት ነገር መክሊቱ ካልሆነ ስኬታማ የመሆን እድሉ ኢምንት ነዉ፡፡

 

          ይሄ መክሊትን ፍለጋ ላይ የቤተሰብ ተፅዕኖም አለበት ለምሳሌ አንዳንድ ቤተሰቦች ልጃቸዉ ጥሩ የንግድ ችሎታ እያለዉ እነርሱ ግን ልጃቸዉን ያለ መክሊቱ ዶክተር ካልሆንክ ብለዉ ማለቂያ የሌለዉ አረንቋ ዉስጥ የሚጨምሩ ፤ ሌሎች አይነት ወላጆች ደግሞ ልጃቸዉ ትምህርት መክሊቱ እንዳልሆነ ተረድተዉ ግን ልጃቸዉ ኮርጆም ቢሆነ ትምህርቱን እንዲጨርስላቸዉ የሚፈልጉ አሉ ፤ ብቻ ይሄ መክሊትን ፍለጋ ብዙ ሰዎች ያልተረዱት ነገር ግን የህይወትን ጓጉንቸር መፍቻ ቁልፍ ነዉ፡፡

          የሰዉ ልጅ ዓላማዬ ብሎ በያዘዉ ነገር ላይ ከፀና እና ከተጋ ብሎም መክሊቱን አዉቆ ከታገለ በተሰማራበት ዘርፍ ምንም እንኳን ቢከብደዉ የማይወጣዉ ደረጃ እና የማይቆናጠጠዉ መቀመጫ የለም፡፡ እኔ በሂወቴ ብዙ ልጆች አጋጥመዉኛል እስከ 12ኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ የዩኒቨርሲቲ ዉጤት አምጥተዉ የሚመርጡትን ዲፓርትመንት ለመምረጥ እና ለመወሰን የተቸገሩ፡፡ መድረሻቸዉን እና ፍጎታቸዉን ሳያዉቁ ነበር የትምህርት መሪያቸዉን ዝም ብለዉ የሚያሾሩት፡፡  እነዚህ ልጆች 12 አመት ሙሉ ሲማሩ ግባቸዉን እና መክሊታቸዉን ገና ያልተረዱ ወይንም በተለያየ ምክንያት መክሊታቸዉን መከተል ያልቻሉ መሆናቸዉ ግልፅ ነዉ ፡፡

          ለአንድ ሀገር ትልቁ መሳሪያዉ የታጠቀዉ ሚሳዔል ወይም የኒኩለር ማብለያዎቹ አይደለም ይልቁንስ እነዚህን የፈጠረዉ ልዐለ ሀያሉ የሰዉ ልጅ አእምሮ ነዉ፡፡ ዉዱ ሀብት አልማዝ ሊመስለን ይችላል እዉነታዉ ግን እሱ አይደለም ዉዱ ሀብት አልማዝን ካለበት ፈልፍሎ እና ቆፍሮ የሚያወጣዉ ብሎም አልማዝን አልማዝ ሆኖ እንዲያምርበት ያስቻለዉ ጥበበኛዉ የሰዉ ልጅ አእምሮ ነዉ፡፡ ይሄ አዕምሮ ግን ፍሬያማ ሊሆን የሚችለዉ መክሊቱን ሲያገኝ ነዉ፡፡ አለበለዚያ በሰዉ መክሊት ዉስጥ ገብቶ ሲባዝቅ ይቀራል፡፡

          ችግኝ ከማልማታችን እና ከመትከላችን በፊት ፤ ለችግኙ የሚቆረቆርለት ማህበረሰብ ልናለማ ይገባል ፤ አለበለዚያ ያ ችግኝ በአመቱ ደርቆ ሌላ ችግኝ እዛዉ ቦታ ላይ መትከላችን የማይቀር ነገር ነዉና፡፡ የሰዉ ልጅ አስተሳሰቡ ከሰለጠነ ለማደግ መንገዱም ጨርቅ ፤ እዳዉም በገብስ ነዉ፡፡ የሰዉ ልጅ ከሰለጠነ በሰዉ መክሊት ገብቶ አይዳክርም የራሱን ለመክሊት ለመፈለግ ይጣጣራል፡፡ ከአለም ሰባቱ ሰዉ አንዱ ቻይናዊ ነዉ ፤ እንግዲህ ይቺ ሀገር ናት ይሄንን ሁሉ ህዝብ ይዛ አሜሪካን የመሰለች የሰለጠነ የዓለም ህዝብ ተዉጣጥቶ የተከማቸባትን ሀገር ደረስኩብሽ እያለች በቁሟ የምታቃዣት፡፡ የቻይና ጉልበቷ ሌላ ሳይሆን ዜጎቿ በመክሊታቸዉ ሀገራቸዉን ስለሚያገለግሉ እና ስለሚተጉ ብቻ ነዉ፡፡

          የሰዉ ልጅ መክሊቱን ከሳደደ የማይወጣዉ አቀበት የማይወርደዉ ቁልቁለት አይኖርም፡፡ የፅናትን ድማሚት ይታጠቃል ያገኛቸዉን መሰናክሎች ሁሉ በያዘዉ ደማሚት ወደ ዶግ አመድነት እየቀየረ ያከስማቸዋል፡፡ ፅኑ ፍላጎት ወደ ስኬት ይጎትተዋል፡፡ ዘፈኝነት ፣ ኳስ ተጫዋችነት ፣ መምህርነት ፣ ኢንጂነርነት ፣ ዶክተርነት ፣ ነጋዴነት ፣ ሹፌርነት ... የእሱ የሆነዉ መክሊቱ እሱነቱን ያነግሰለታል፡፡

          መጀመሪያ መክሊታችንን ካወቅን እንደ ፌስቡኩ ፖስት ስራ ስናፈላልግ አንገኝም፡፡ መክሊታችን ወደ ፍላጎት ይገፋናል ፤ ዉስጣዊ ፍላጎት ካለን ደግሞ ችግር በበዛባት ሀገር ዉስጥ እንደመኖራችን ችግሮችን ለመፍታት አንሞክራለን ፤ በተግባር ሲታገዝ ደግሞ መክሊታችን እዉን ሆኖ ስራ ሲፈጥርልን እና የኔ የምንለዉን ነገር ሲያሳቅፈን እናየዋለን፡፡

          የሰዉ ልጅ ግንባሩን የሚቋጥርለት ፣ ሽንጡን የሚገትርለት ፣ መስዋዐትነት የሚከፍልለት ፣ የህይወቱን ጣዕም የሚያጣጥምበት መክሊት ሊኖረዉ ይገባል፡፡

 

ቆየት ያለች ጥዑም ዜማ -

ሰዉ ከተሰማራ

 እንደ እየ ስሜቱ

በዋለበት ፤ ባደረበት

 አይቀርም ማፍራቱ …

.

.

.

አዎን … አይቀርም ማፍራቱ ፡፡


Reviews

Post Comment