የሳይበሩ ሩጫ
ኮምፒዉተርን መሰረት ያደረገ ኑሮ መኖር ካደረግን ሰንበትበት ብለናል፡፡ ወደንም ይሁን ሳንወድ ጥገኞች እየሆንን እንገኛለን ፤ ብዙ ኮምፒተሮች አንድ ጋር ተጣምረዉ ደግሞ በኢንተርኔት አማካኝነት ግንኙነት በማድረግ ህይወትን ቀላል እያደረጉልን ይገኛሉ ፤ ይሄንን ስብስብ ሲስተም ሰንል እንጠራዋን፡፡ እነዚህ የኮምፒዉተር ሲስተሞች ዉጪ ሀገር ካሉ ቤተሰቦቻችን ጋር ፊት ለፊት ለማዉራት ከማስቻል ጀምሮ እስከ ገንዘባችንን በፈለግንበት ቦታ ሰዓት ማንቀሳቀስ እንድንችል አድርገዉናል፡፡ በተገቢዉ አገልግሎት ካሰጡን ደግሞ ህይወታችን ሲስተጓጎል ይታያል፡፡ ለምሳሌ አብዛኛዉ ሰዉ ከሚጠላቸዉ ቃል አንዱ የሆነዉ ሲስተም ጠፍቷል የሚለዉን እየሆነ መጥቷል ፣ ባንክ ላይ ሄደን ሲስተም ከሌለ ብራችንን መጠቀም አንችልም ፣ ቀበሌ ሄደን ሲስተም ከተቋረጠ ጉዳያችንን ሳንጨርስ አራዝመን እንመለሳለን ፣ ከዚህም ከፍ እያለ ደግሞ የጤና መረጃዎቻችን ሲስተም ላይ ሲቀመጡ ድንገተኛ እንኳን ታመን ሄደን ሲስተም ሲቋረጥ የበፊት መረጃችንን ማግኘት ይሳነናል ፣ ፈተና ልንፈተን ሄደን ሲስተም የለም ተብለን እንመለሳለን፡፡ ስለ ጊዜያዊ ትንሹ የሲስተም መቋረጥ ምን ያህል አደጋ እንዳለዉ ለማንሳት የሞከርኩት አለምን እየተፈታተናት ስላለዉ የሳይበር ጥቃት ለማዉጋት እያኩበኩብኩኝ ስለሆነ ነዉ፡፡
በ1988 ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ የሳይበር ደህንነት የሚለዉ ቃል ጥቅም ላይ የዋለዉ፡፡ ምከንያቱ ደግሞ በአሜሪካ 60 000 ኮምፒዉተሮችን በአንድ ጊዜ ከጥቅም ዉጪ ለማድረግ ያጠቃዉ ወርም ነበር፡፡ የሳይበር ደህንነት ትርጉሙም በኢንተርኔት አማካኝነት የተያያዙ የክፍያ ስርዓቶችን ፣ ዌብሳይቶችን ፣ የግለሰብ መጠቀሚያ አካዉንቶችን ፣ የመሰረተ ልማቶችን ኢላማ ያደረግ ጥቃትን መከላከል መቻል ነዉ፡፡
የሳይበር ጥቃት ህገወጥ በሆነ መንገድ ኢንተርኔትን እና ኮፒዉተሮችን አጣምሮ እዉቀትን በመጠቀም ያለ ፈቃድ መረጃ መመዝበር ከዚህም ሲያልፍ ከጥቅም ዉጪ ማድረግ ነዉ፡፡ በየአመቱ ከ 1 ዜታባይት በላይ የዲጂታል መረጃዎች ይዘዋወራሉ፡፡ አብዛኞቹ ጥቃቶችም እነዚህ መረጃዎችን ማግኘት ላይ ትኩረቶቻቸዉን ያደርጋሉ፡፡
ለሳይበር ጥቃት እንደ መሳሪያነት የሚያገለግሉ ለዚህ ድርጊት ታልመዉ የሚዘጋጁ የኢንተርኔት ቫይረሶች እና ወርሞች ሲሆኑ ከሚተላለፉባቸዉ መንገዶ ዉስጥም እንደ ፍላሽ ያሉ መጠቀሚያዎች ፣ ፋይል ከኢንተርኔት ዳዉንሎድ በሚደረግበት ጊዜ እና የኢሜይል አታችመንት ፋይል ሲላክ አብረዉ በመቀላቀል ዋናዎቹ መንገዶች ናቸዉ፡፡
የሳይበር ደህንነት ጥቃት አይነቶች
የሳይበር ጥቃት እዉቀቱ እና ችሎታዉ ያላቸዉ ኤክስፐርቶች የተለያዩ ሶፍትዌሮችን በመጠቀም የሚያደርጉት የዘመኑ ፍልሚያ ነዉ፡፡ እነዚህም የተለያየ አይነት ስያሜ እና ቅርፅ ሊኖራቸዉ ይችላል -
- ዲኒያል ኦፍ ሰርቪስ (Denial of Service) - አንድ ትልቅ ሰርቨር ኮምፒዉተርን የተለያዩ ሶፍትዌሮችን በመጠቀም እጅግ ብዙ መረጃዎችን በመለክ ማጨናነቅ እና ኢላማ ዉስጥ ያለዉንም ኮምፒዉተር ከአቅም በላይ ሲሆንበት ስራ እንዲያቆም በዚያም ምክንያት ከጥቅም ዉጪ ማድረግ ነዉ፡፡
- ዲትሪቢዉትድ ዲኒያል ኦፍ ሰርቪስ (Distributed Denial of Service) - ይሄም በተመሳሳይ እጅግ ብዙ መረጃዎችን በመላክ ኢላማ ውስጥ የገባዉን ኮምፒዉተር ድምጥማጡን ማጥፋት ሲሆን ልዩነቱ ጥቃቱ እና መረጃዎች የሚመጡት ከተወሰኑ ኮመፒዉተሮች ሳይሆን ብዙ ቀድመዉ በተጠቁ ዞምቢ ኮምፒዉተሮች በመታገዝ ነዉ፡፡ በየቀኑ ከ150 000 በላይ ኮምፒዉተሮች ምናልባትም የእኛን የግል ኮምፒዉተር ጨምሮ የዞምቢይ ጥቃት ሰለባ ይሆናሉ፡፡ እኛም ኮምፒዉተራችን ሰለባ ይሁን አይሁን ሳናዉቅ ሀከሮች ግን ኢንተርኔት ላይ ስንሆን የኛን ኮምፒዉተር ሌሎች አገልግሎቶችን ለማጥቃት ይጠቀሙባቸዋል፡፡
- በቫይረስ (Virus) - ከተለያዩ ፋይሎች እና ፕሮግራሞች ጋር ራሱን በመቀላቀል ከአንዱ ኮምፒዉተር ወደ ሌላ ኮምፒዉተር እንዲተላለፍ በማድረግ ጥቃትም እንዲፈፅም የሚያደርግ ነዉ፡፡
- ዎርም (Worm) - ከቫይረስ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ልዩነቱ ወርም ራሱን ቶሎ ቶሎ በማባዛት ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርስ በተጨማሪም ከአንድ ወደ አንድ ኮምፒዉተር ያለ ቀጥተኛ ሰዉ ንክኪ መተላለፍ ይችላል፡፡
- ስፓም (Spam) - በጣም ብዙ ኢሜይሎችን እና መረጃዎችን በዉስጣቸዉ ድብቅ አደጋ በመያዝ የብዙዎችን ኢሜይሎች እና ኮምፒዉተሮች ሰለባ እያደረገ የሚገኝ የጥቃት አይነት ነዉ፡፡
- ትሮጃን ሆርስ (Trojan Horse) - በጣም ጠቃሚ የሆኑ አፕሊኬሽናች ዉስጥ ራሱን እንዲደብቅ ተደርጎ ሰዎች አፕሊኬሽኑን ጭነን ስንጠቀም ትሮጀን ሆርስም አብሮ ጥቃቱን ይጀምራል፡፡
- ኪይ ሎገር (Key logger) - ይሄኛዉ ደግሞ ከላይ ካሉት ጥቃት ለየት የሚያደርገዉ ቀጥተኛ ጉዳት ከማድረስ ይልቅ ልክ እንደ ሰላይ ያለ እኛ እዉቅና እያንዳንዷን እንቅስቃሴዎቻችንን ከኮምፒዉተር ላይ እየመዘገበ የሚያስተላልፍ አደገኛ ሶፍትዌር ነዉ፡፡
ሳይበር ምን ያህል ያሳስባል ?
እኛ ጎግልን መረጃዎችን ለመፈለግ እንደምንጠቀምበት ሁሉ ሾዳን የተባለዉ ብሮዉዘር በዓለም ላይ ያሉ ተጋላጭ የሆኑ ኔቶርክ እና ሲስተሞችን ቁልጭ አድርጎ ለሀከሮች የሚያሳይ ነዉ፡፡ በዚህም ብሮዎዘር ላይ እንደሚታየዉ አብዛኛዉ የአለም ኔቶርክ ለጥቃት ተጋላጭ ነዉ፡፡
እኛ ገና በአግባቡ ወደ ሰለጠነዉ ዓለም ስላልተቀላቀልን ያን ያህል ሀሳብ አልሆነብንም እንጂ ዓለም እንቅልፍ ካጣች ሰነባብታለቸ፡፡ ነገሮች ሁሉ ወደ ሲስተምነት እየተቀየሩ በመጡባት ዓለም መረጃዎችን ከጥቃት መከላከል ትልቁ ፈተና እየሆነ መጥቷል፡፡ የአለም ትልልቅ የደህንነት እና የስለላ ቢሮዎች ትኩረታቸዉን ወደ ሳይበር ካዞሩ ሰነባብተዋል፡፡ እንደ የአሜሪካዉ ሲአይኤ ፣ የእስራኤሉ ሞሳድ የራሺያዉ ኬጂቢ በተጨማሪም የቻይና ፣ ሰሜን ኮርያ እና እንግሊዝ የመሰሉ የአለም ቁንጮ ሀገራት የስለላ ድርጅቶች አንዱ የአንዱን ድክመት በመጠቀም ሀያልነታቸዉን ለማስከበር ደፋ ቀና እያሉ ናቸዉ፡፡ በኛም ሀገር ምንም አንኳን ኢትዮጵያ ሳታላይት ልታመጥቅ መሆኑን ስንሰማ ብዙዎቻችን ሆዳችን ሳይሞላ ብለን የጮህንባት ሀገር ብትሆንም ኢንሳ ብቀጥንም ጠጅ ነኝ ፣ ብዙ ጥቃቶችን መልሻለሁ እያለን ይገኛል፡፡ እንደዚህም ቢሆን ገና በብዙ ርቀት ሀገራችን ዉስጥ ግንዛቤዉ እና ትኩረቱ ይቀራል፡፡ የታለመ ከባድ ጥቃት ቢፈፀምብን የመከላከል አቅሙ ይኖረናል ብሎ ማሰብ ከባድ ነዉ፡፡
አሜሪካ በየአመቱ ከምታወጣቸዉ በጀቶች ዉስጥ ከፍተኛዉን ጉርሻ ሳይበር ይወስዳል፡፡ በዚህ በሰለጠነ ዘመን መረጃን መደበቅ የማይቻልበት ዘመን ሆኗል፡፡ አንድ ሀገር የሌላዉን ሀገር መረጃ በመመንተፍ መረጃ ጠላፊዉ ከተጠቂዉ ሀገር በላይ ስለ ሀገሪቱ ግንዛቤ እንዲኖረዉ ይጥራል፡፡ አሁን ማን ያምናል አስፈሪዉ እና ታላቁ ሞሳድ ከኢትዮጵያዉያን በላይ ስለ ኢትዮጵያ አጠቃላይ ሁኔታ ፤ በተጨማሪም ክስተቶች የተተነተነ እና በቂ መረጃ አለዉ ቢባል፡፡በዘመነ ኢንተርኔት ምንም የሚደበቅ ነገር አይኖርም ፤ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችን እንደ አሜሪካ ያሉ ባለ ፈርጣማ ጡንቻ ሀገራት ባስወነጨፏቸዉ ሳቴላይቶች ቁጥጥር ስር ከዋለ ሰነባባቷል፡፡
የሳይበሩ አስፈሪ ንጉሶች
የ24 ዓመቱ አልጀሪያዊ ሀምዛ ቤንዴላጂ እጅግ አስፈሪ ግለሰብ ነበር ፤ ከ217 በላይ የዓለም ባንኮችን ብቻዉን ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የመዘበረ ሰዉ ነዉ፡፡ እጅግ ብዙ አየር መንገዶች ሳይከፍል በፓስፖርት የተጓዘ መረጃ ጠላፊ፡፡ ይሄ ሰዉ የመዘበረዉን ብር ሙሉ ለሙሉ ለአፍሪቃዉያን እና ለፍልሰጤሞች በእርዳታ ለግሷል፡፡ በመጨረሻም ምንም እንኳን ብዙዎች ቢከራከሩለትም አሜሪካ ጥፋተኛ ነህ አልምርህም ብላ በሞት ስቅላት እንደቀጣችዉ የሚሳይ ምስል አስተላልፋለች ፤ ሀከሩም ሲሰቀል ፊቱ ላይ ከፍተኛ ፈገግታ የሚታይበት ምስል ይፋ ተደርጓል፡፡ አሁንም ቢሆን ምስሉን የሚጠራጠሩ ሀምዛ እንዳልሞተ እና አሜሪካ በድብቅ እያሰራችዉ እንደሆነ የሚከራከሩ ሰዎች አሉ፡፡
አኖነይመስ የተባለዉ ማንነታቸዉ በግልፅ የማይታወቁ በተለያዩ ዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ የሀከሮች ስብስብ ሲሆን እስካሁን ድረስ በብዙዎች በመፈራት እና ብዙ መረጃዎችን በመመዝበር የሚስተካከለዉ የለም፡፡ ይህ ቡድን መንግስታዊ እና የኮርፖሬት ድርጅቶችን እንቅልፍ ከነሳቸዉ ሰነባብቷል፡፡
ጆናትን ጀምስ የ15 ዓመት ታዳጊ እያለ የናሳ እና የአሜሪካ መከላከያ ዲፓርትመንትን ሀክ አድርጓል፡፡ይሄም ጆናታንን በእድሜ ትንሹ ትልቅ ድርጅቶችን ያጠቃ ሀከር አድርጎታል፡፡ ጆናታን ከናሳ 13 ኮምፒዉተሮችን መጠቀም ሲችል ከ 2 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመቱ ሶፍትዌሮችን እና መረጃዎችን መዝብሯል፡፡ በዚህም ምክንያት ሲስተሙ ለ21 ቀናት ሲቋረጥ ይሄንንም ለመመለስ ከ40 000 ዶላር በላይ ወጪ ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጆናታን የአሜሪካን መከላከያ ዲፓርትመንት በተለይም የመከላከያ አደጋ መቀነስ ኢጀንሲን በመስበር የመጀመሪያዉ ሀከር ሲሆን ይሄም አሜሪካ ሊገጥሟት የሚችሉ አደጋዎች የሚመዘገብበት አንደመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ እየተደረገበት ሾልኮ መረጃ መዝረፉ አስደናቂ አድርጎታል፡፡ ጆናታን ምንም እንኳን ህፃን ስለነበር በአሜሪካ ህግ ከ6 ወር ከኮምፒዉተር መራቅ ያለፈ ከባድ እርምጃ ባይወሰድበትም ከ 10 ዓመት በኋላ በ25 ዓመቱ ራሱን ከዚህ ድርጊት ማቀብ ባለመቻሉ ራሱን በራሱ ሊያጠፋ ችሏል፡፡
የመረጃ ምዝበራዎች እና የካምፓኒዎች ዉድመት እዉነታዎች
በ2010 እና በ2015 መካከል ያለዉን ልዩነት ብንመለከት የሀኪንግ እና መረጃ ምዝበራ እዳ በ176 በመቶ ጭማሬ አሳይቷል፡፡ በ2018 ብቻ ደግሞ ዲስትሪቢዉትድ ዲኒያል ሰረቪስ በ500 ፐረሰንት ጨምሮ ታይቷል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ የኮምፒዉተር ወርም የተፈጠረዉ እኤአ በ1979 ሲሆን የኮምፒዉተር ቫይረስ ደግሞ 1983 ነዉ፡፡አይ ላቭ ዩ የተሰኘዉ ቫይረስ በ2000 እኤአ ዓ.ም በ 2 ቀን ብቻ ከ45 ሚሊዮን በላይ ኮምፒዉተሮችን በማጥቃት ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ በዚሁ ቫይረስ አማካኝነት በ ጃንዋሪ 25 2003 የዓለም መገናኛ ኢንተርኔት ተቋርጦ ነበር፡፡
በ2009 በዩኤስኤ ብቻ ከ222 ሚሊዮን በላይ መረጃዎች ድምጥማጣቸዉ ጠፍቷል ፤ ይሄም የኦባማን መንግስት ከእንቅልፉ ቀስቅሶ ወደ ጠንካራ እርምጃ እንዲገባ አስገድዶታል፡፡ በአንድ ጊዜ ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ በአንድ ጥቃት ብቻ ከኤትኤም መዘረፉም የቅርብ ጊዜ ትዉስታችን ነዉ፡፡
ታዋቂ የኢሜይል አገልግሎት ሰጪ የሆነዉ ያሁ ከቢሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች አካዉንት ተመዝብሯል ወይንም ሀክ ተደርጓል፡፡ ይሄም ሀያልነቱን ለጂሜይል እንዲያስረክብ አስገድዶታል፡፡
ከስራ ጋር ተያያዥ የሆነዉ ሁላችንም የምንጠቀምበት የሊንክድ ኢን የሶሻል ሚዲያ ከ167 ሚሊዮን በላይ አካዉንቶች መረጃ በጠላፊዎች ተመዝብሮበታል፡፡
ሁላችንም በምንጠቀምበት በዓለም ላይ ከ2 ቢሊዮን በላይ ተጠቃሚ ባሉት ፌስቡክ እንኳን በየቀኑ ከ160 000 በላይ አካዉንቶ ሀክ ይደረጋሉ፡፡
ድሮፕ ቦክስ መረጃዎቻንን ክላዉድ ላይ እንድናስቀምጥ የሚያስችለን ፕላትፎርም ሲሆን፡፡ የ68 ሚሊዮን ድሮፕ ቦክስ አካዉንቶች ከነመረጃዎቻቸዉ የጥቃት ሰለባ ሆነዋል፡፡
በ2011 የሶኒ የጌም ኔቶርክ በደረሰበት ጥቃት ከ77 ሚሊዮን በላይ ደንበኞቹን መስተጓጎላቸዉ እና ከፍተኛ ዉድመት መድረሱ በተጨማሪም በዚሁ ዓመት የሲአይኤ ዌብሳይት እና ሲስተም አገልግሎት ለማቆም ተገደዉ ነበር፡፡
የታዋቂዉ ድርጅት አፕል አይክላዉድ መረጃ ማከማቻ በ2014 በደረሰት ጥቃት ብዙ መረጃዎች ተመዝበረዋል፡፡ ከ200 በላይ እዉቅ አሜሪካዉያን ያልተፈለጉ ምስሎች እና ፎቶዎችን ጨምሮ በአደባባይ ከስልኮቻችዉ ተሰርቀዉ ለህዝብ ይፋ ተደርገዉባቸዋል፡፡
የሳይበር ጥቃቶች ከመረጃ ምዝበራ በተጨማሪ አሁን ላይ ትኩረታቸዉን ወደ ዉሀ ፤ ባቡር ፤ ጋዝ እና ኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ አነጣጥረዋል፡፡በአሜሪካ የኢነርጂ ዲፓርትመንት ላይ በተለይም ከቻይና ፤ ሰሜንኮርያ እና ራሺያ ያነጣጠሩ በየቀኑ ከ10 ሚሊዪን በላይ ጥቃቶች ይሰነዘራሉ፡፡
በ2009 ተደረገ ሌላ ጥናት ከ60 በመቶ በላይ ተቀጣሪ ድርጅቶቻቸዉን ሲለቁ የመረጃ ስርቆት ይፈፅማሉ፡፡ ይሄም ተጋላጭነቱን ይጨምረዋል፡፡ በአማካይ አንድን ሀክ የተደረገ ነገር መፍትሄ ለመስጠት 170 የስራ ቀናተን ይፈጃል፡፡
በጁሊያን አሳንጅ የተመሰረተዉ ዊኪ ሊክስ የተመዘበሩ መረጃዎ የሚለቀቁበት ሳይት ሲሆን ጁሊያን ምንም አይነት የግል የሚባል መረጃ የለም ሁሉም ለጥቃት የተጋለጠ እና በሀከሮች እጅ ስር የሆነ ነዉ ይላል፡፡
እንዴት ራሳችንን ከሳይበር እንከላከል?
ሀከሮች በግለሰብ ደረጃ የሚያደርጉት አስፈላጊ የሆኑ እንደ ኢሜይል ፤ የክፍያ ፓስዎርዶች አይነት መረጃዎችን ከሞጨለፉን በኋላ ይደብቁብናል ፤ በመቀጠልም በምንያህል ዋጋ ሊመልሱልን እንደሚችሉ ይደራደራሉ ፤ በመጨረሻም በገዛ ንብረታችን ክፍያ ስንፈፅምላቸዉ መልሰዉ ንብረታችንን ይልኩልናል፡፡ ይህ በብዙ ሀገራት የተለመደ ሲሆን በኢትዮጵያም በጥቂት ዓመት ዉስጥ ወረረሽኝ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡ ስለሆነም እያንዳንዳችን ራሳችን ከሳይበር ጥቃት ለመከላከል የሚከተሉት አርምጃዎች መዉሰድ አለብን -
- ፓስዎርድ ስንጠቀም ፊደላትን ፣ ቁጥሮችን ምልክቶችን አቀላቅሎ በጣም ጠንካራ ፓስወርድ እንዲኖረን ያስችለናል፡፡
- ለተለያዩ አካዉንቶች የተለያዩ ፓስወርዶችን መጠቀም አንዱ ሀክ ቢደረግ የሌላዉን ያድንንልናል፡፡
- የማይገመቱ ረዘም ያሉ ፓስዎርዶችን መጠቀም ፤ ባለ 6 ሆሄ ብቻ ሲሆን በ10 ደቂቃ ዉስጥ ሀክ ሊደረግ ሲችል ፤ ሁለት ፊደል እና ቁጥሮችን ብንጨምር ግን ሀኪንጉ እስከ 3 አመት ሊፈጅ ይችላል፡፡
- እንደ ዌብ ካም ፣ ቴሌቪዥኖቻችን እና የኮምፒዉተሮቻችን ካሜራዎች ከኔቶርክ ጋር ሲያያዙ በጥንቃቄ እና አስፈላጊ በሆኑ ሰዓታት ብቻ መጠቀም ፤ አለበለዚያ የተደበቁ ድርጊቶቻችን በሌሎች እይታዎች ስር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
- በተለይ እንደ ቻይና ያሉ ሀገራት በሚያመርቷዉ ምርቶች ላየ ደግሞ ሰፕላይ ቼይን የሚባል የጥቃት አይነት አለ ይሄ ጥቃት የሚሰነዘረዉ እንደ ሞባይል ስልክ ፣ ካሜራ እና ሰርቨር የመሳሉትን እቃዎች ስንገዛ አምራቾች ለስረቆት የሚያገለግላቸዉን በጣም ትንንሽ ችፖች አብረዉ ይቀብራሉ ስለዚህ የኛ የምንለዉ ስልክ ያለ እኛ እዉቅና በአንድ ጊዜ ሌሎች ሰዎች ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ ስለዚህም የምንገዛችዉ ስልኮች ከታወቁ እና አስተማማኝ ካምፓኒዎች ቢሆን ይመረጣል ፡፡
- በአካዉንታችን እንደ 2 ስቴፕ ቬሪፊኬሽን ያሉ መንገዶችን መጠቀም አካዉንታችን ፓስዎርድ ከመቀየሩ በፊት እዉቅና እንዲኖረን ያስችለናል፡፡
- ዋይፋይ ኔትዎርክ ኮኔክት ከማድረጋችን በፊት ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ
አላስፈላጊ የሆኑ ምስሎችን እና መልዕክቶችን አለመላላክ ፤ ምክንያቱም መልዕክቶቹ ከላክንለት ሰዉ ዉጪ በኔቶርክ ላይ እያሉ ሌሎች ሰዎች ጋር በቀላሉ ሊገቡ ስለሚችሉ፡፡ - አፕሊኬሽኖቻችን አፕዴት ማድረግ ፤ አንዲሁም ከአምራቾቻቸዉ በቀጥታ ዳዉንሎድ ማድረግ ተያይዘዉ ከሚመጡ ጥቃቶች ይሰዉሩናል፡፡
- የአሚይል መልዕክቶችን ከመክፈታችን በፊት የላኪዉን አድራሻዉ ማረጋገጥ፡፡
- ሰራተኞቻችን ከድርጅቶቻችን ሲለቁ አካዉንታቸቸዉን ወዲያዉኑ ማስወገድ፡፡
- እንደ ኬይ ሎገር ያሉ ሶፍትዌሮች ሰዎች እንዳይጭኑብን ኮምፒዉተራችንን አሳልፈን አለመስጠት፡፡
- በተቻለ መጠን ብሮዉዘራችን ላይ ፓስዎርድ ሴቭ አለማድረግ ምክንያቱም የኮምፒዉተሩን ፓስዎርድ የሚያዉቅ ሰዉ ሁሉ ፓስዎርዶቻችንነ ሊያገኛቸዉ ስለሚችል፡፡
- ለቴክኒካል ሰዎች ደግሞ ኔቶርካችንን በፋየር ዋል መገደብ ይኖርብናል፡፡
የሳይበር ስፔሻሊስቱ የሂልኮ ባለቤት እና መስራች ዶ/ር አህመድ ሰይድ በአንድ ወቅት በቴክ-ቶከ ሰለሞን ሾዉ ላይ ቀርበዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ምንም እንኳን ከፍተኛ የአይቲ ሲስተም ዝርጋታ መስፋፋት ቢኖርም በደህነቱ ላይ በቂ የሆነ ስራ እየተሰራ እየደለም፡፡ ግንዛቤዉ በጣም ገና ነዉ ግንዛቤዉም ያለበት ቦታ ወደ ትግበራ ለመሄድ እጅግ መዘግየት ይታይል፡፡ ኤትኤም ፣ ፔይመንት ካርዶች ፣ ተጋላጭነታቸዉ ይጨምረዋል፡፡ ጥቃት ደርሶብናል አልደረሰም የሚለዉን እንኳን ማወቅ የሚቻልበት ሁኔታ ዉስጥ አይደለንም ፤ ሲሉ ተደምጠዋል ስለዚህ ነገ ከማዘን ዛሬ ደህንነታችን እንጠብቅ፡፡
በብሩክ ማሞ
Post Comment